በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ የካዛክስታን ሪፑብሊክ ወታደራዊ ፍርድ ቤት። ውስጠኛው ፎቶ፦ ኅዳር 2023 እና ሚያዝያ 2024 በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት አለመስጠትን በተመለከተ የተላለፉት ብይኖች ቅጂዎች

ግንቦት 31, 2024
ካዛክስታን

በካዛክስታን በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ያለመስጠትን መብት የሚያስከብር ታሪካዊ ውሳኔ ተላለፈ

በካዛክስታን በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ያለመስጠትን መብት የሚያስከብር ታሪካዊ ውሳኔ ተላለፈ

ካዛክስታን ውስጥ በሃይማኖታዊ እምነት ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆንን በሚመለከት የተላለፈ ውሳኔ ግንቦት 23, 2024 ተግባራዊ ተደርጓል። ውሳኔው የ20 ዓመት ወጣት ከሆነው ከወንድም ዳኒል ስማል ጋር የተያያዘ ነበር፤ ዳኛው ጉዳዩን “በጣም አስገራሚ” ሲሉ ገልጸውታል።

ግንቦት 17, 2023 ማለትም ይህ ውሳኔ ከመተላለፉ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ዳኒል ወደ አውራጃው ወታደራዊ ምልመላ ቢሮ ተጠርቶ ነበር። እሱም ሃይማኖታዊ አቋሙን በአክብሮት አስረዳ። ከዚህም በተጨማሪ ዳኒል በሃይማኖታዊ አቋሙ ምክንያት ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ መሆን እንደሚችል የሚያረጋግጥ መንግሥታዊ ሰነድ ለመልማይ መኮንኖቹ ቀርቦላቸው ነበር። ሆኖም መልማይ መኮንኖቹ ዳኒል ያቀረበላቸውን ጥያቄ ችላ በማለት ለወታደራዊ አገልግሎት መለመሉት። በቀጣዩ ቀን ባለሥልጣናቱ ዳኒልን በማስገደድ ከመኖሪያ ከተማው ሩድኒ 2,000 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ወታደራዊ ማዕከል በባቡር ላኩት። ሆኖም ዳኒል በዚህ አስቸጋሪ ወቅትም እንኳ ወታደራዊ ቃለ መሐላ ለመግባት፣ የደንብ ልብስ ለመልበስ ወይም በሥልጠና ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆኑን በአክብሮት በመግለጽ ገለልተኛ አቋሙን ጠብቋል። ዳኒል ቅሬታውን በተገቢው መንገድ በተደጋጋሚ ጊዜያት ለተለያዩ ባለሥልጣናት ያቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፤ በመሆኑም መፍትሔ ለማግኘት ወደ ፍርድ ቤት አቤት አለ። ጉዳዩም ለሦስት ወራት በችሎት ፊት ሲታይ ቆየ።

ኅዳር 2023 ወንድም ዳኒል ስማል በአልማቲ ጦር ሰፈር ወታደራዊ ፍርድ ቤት ደጅ ላይ ቆሞ

በመጨረሻም ኅዳር 9, 2023 የአልማቲ ጦር ሰፈር ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኒል ለውትድርና መመልመሉ ሕጋዊ እንዳልሆነ የሚገልጽ ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል መግለጫ አስፍሯል፦ “[ዳኒል] ሃይማኖታዊ እምነቱ በወታደራዊ አገልግሎት እንዲሳተፍ እንደማይፈቅድለት በግልጽ ተናግሮ ሳለ ለወታደራዊ ግዳጅ መመልመሉ የሕሊና ነፃነቱንና ሃይማኖታዊ መብቱን የሚጋፋ ነው።” በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ዳኒል ለስድስት ወራት እንዲቆይ ከተገደደበት ወታደራዊ ተቋም እንዲለቀቅ አዟል።

ፍርድ ቤቱ ብይን ካስተላለፈ ብዙም ሳይቆይ ወታደራዊ ባለሥልጣናቱ ይግባኝ አሉ። ነገር ግን ሚያዝያ 16, 2024 የአገሪቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የሆነው የካዛክስታን ሪፑብሊክ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ታችኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጸደቀው። ግንቦት 23, 2024 ተግባራዊ የተደረገው ይህ ታሪካዊ ውሳኔ፣ የዜጎች የሕሊና ነፃነት እንዲከበር የሚያዙትን ዓለም አቀፋዊ ሕጎችንና የካዛክስታንን ሕገ መንግሥት ያጣቀሰ ነበር። ፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል መግለጫ አስፍሯል፦ “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን መንግሥት አንድን ግለሰብ ሕሊናው የማይፈቅድለትን ነገር እንዲያደርግ የማስገደድ መብት የለውም።”

በካዛክስታን የሚገኝ ፍርድ ቤት ግለሰቦች በሃይማኖታዊ እምነታቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ያለመስጠት መብት እንዳላቸው በማያሻማ ሁኔታ እውቅና ሲሰጥ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በካዛክስታን የይሖዋ ምሥክሮች ቃል አቀባይ የሆነው ወንድም ሌቭ ፍላዲሼቭ እንዲህ ብሏል፦ “ፍርድ ቤቶቹ ወንድም ዳኒል በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ያለመስጠት ሕጋዊ መብት እንዳለው ግልጽ በማድረጋቸው አመስጋኞች ነን። ብይኑ በካዛክስታንና በመካከለኛው እስያ አገራት መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶች ለማስጠበቅ መሠረት የሚሆን ትልቅ እመርታ ነው።”​—1 ጢሞቴዎስ 2:1