በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

(በስተ ግራ) በአካባቢው በሚገኝ የኪራይ አዳራሽ ውስጥ የተካሄደው የውሰና ፕሮግራም። (በስተ ቀኝ) በአዲሱ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙት ሁለት ሕንፃዎች

ኅዳር 19, 2019
ኬንያ

በኬንያ አዲስ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤት ተወሰነ

በኬንያ አዲስ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤት ተወሰነ

ኅዳር 9, 2019 ኬንያ ውስጥ በምትገኘው በኤልዶሬት ከተማ አንድ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተወሰነ። የኬንያ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ቤንት ኦልሰን 1,199 ለሚሆኑ ተሰብሳቢዎች የውሰና ንግግር ሰጥቶ ነበር፤ ከእነዚህ ተሰብሳቢዎች መካከል 500 ገደማ የሚሆኑት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው። የ433 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት እና ለወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀው ትምህርት ቤት ይካሄዳል። ይህ ትምህርት ቤት፣ በዓመት ቢያንስ አራት ጊዜ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አስተምሮ እንደሚያስመርቅ ይጠበቃል።

ትምህርት ቤቱ፣ የቅርንጫፍ ቢሮው ንብረት የሆኑ ሕንፃዎችን በማደስ የተሠራ ነው። ቀደም ሲል የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት የነበረ አንድ ሕንፃ የትምህርት ቤቱ የልብስ ማጠቢያ ክፍል፣ ኩሽና እና የመመገቢያ ክፍል እንዲሆን ተደርጎ ታድሷል። አንድ የስብሰባ አዳራሽ ደግሞ ትምህርት የሚሰጥበት ክፍል እንዲሆን ተስተካክሏል። ሥራው የተጀመረው ሚያዝያ 1, 2019 ሲሆን አብዛኛው ሥራ እስከ መስከረም 9 ድረስ ተጠናቋል።

ወንድም ቤንት ኦልሰን፣ ትምህርት ቤቱ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ እንዲህ ሲል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኘው ክልል ውስጥ ከፍተኛ እድገት እንደሚኖር እንጠብቃለን። በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የሚሰጠው ሥልጠና ወደፊት የምንጠብቀውን እድገት ለማስተናገድ ይኸውም ወደ ይሖዋ ተራራ የሚጎርፉትን ሕዝቦች ለመርዳት በሚደረገው ጥረት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው እርግጠኞች ነን።”—ሚክያስ 4:1