በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የኬንያ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ

ሰኔ 7, 2022
ኬንያ

የኬንያ መንግሥት የተማሪዎችን መብት የሚያስከብር መመሪያ አወጣ

የኬንያ መንግሥት የተማሪዎችን መብት የሚያስከብር መመሪያ አወጣ

የኬንያ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የትምህርት ቤት የአስተዳደር አካላት የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ መብት እንዲያከብሩ የሚያዝዝ መመሪያ በቅርቡ አውጥቷል። መመሪያው የወጣው መጋቢት 4, 2022 ነው። ይህ መመሪያ፣ ለብዙ ዓመታት መድልዎ ሲደረግባቸው የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች መብት እንደሚያስከብር ተስፋ እናደርጋለን።

ከ2015 ወዲህ 36 የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ከትምህርት ቤት ተባርረዋል ወይም ጊዜያዊ እገዳ ተጥሎባቸዋል፤ ይህ የሆነው በትምህርት ቤቱ ውስጥ ግዴታ በሆኑ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው። በ2018 በናይሮቢ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች፣ ይህን ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ማስቆም ስለሚቻልበት መንገድ ከኬንያ የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ነበር። ለአብነት ያህል፣ ጥቅምት 23, 2018 የቅርንጫፍ ቢሮው ተወካዮች በወቅቱ የትምህርት ካቢኔ ጸሐፊ ከነበሩት ከዶክተር አሚና መሐመድ ጋር ተገናኝተው ነበር።

መንግሥት ያወጣው መመሪያ፣ በኬንያ ያሉ አንዳንድ “የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎችና የሥራ ኃላፊዎች . . . በማይረቡ ምክንያቶች የተነሳ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው እንደሚያፈናቅሉ” በይፋ ገልጿል። መመሪያው አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ መብት እየተጋፉ ነው፤ ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎችን ለመቀበል ወይም ከትምህርት ቤት ለማባረር ሃይማኖትን ምክንያት እያደረጉ ነው።”

መመሪያው “ሃይማኖታዊ መብትን መጋፋት ከተለያዩ ብሔራዊ ሕግጋት እንዲሁም ከክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች . . . በተለይ ደግሞ ከኬንያ ሕገ መንግሥት ጋር የሚጋጭ ተግባር” እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቶ መግለጹን የኬንያ የዜና ተቋማት በስፋት ዘግበዋል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች “ከሃይማኖታቸው ጋር በሚጋጭ ድርጊት” እንዲካፈሉ መጠየቅ የለባቸውም። መመሪያው የሚደመድመው ሁሉም የትምህርት ቤት የአስተዳደር አካላት ይህን አካሄድ እንዲከተሉ ጥያቄ በማቅረብ ነው።

ኪምበርሊ ንያንጌት በናይሮቢ የምትኖር የ17 ዓመት ወጣት ናት፤ ይህች የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “በሃይማኖታዊ አቋሜ የተነሳ ትምህርት ቤቱ ከአምስት ጊዜ በላይ ወላጅ እንዳመጣ አድርጎኛል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋማችንን የሚደግፍ እንዲህ ያለ መመሪያ በመውጣቱ ደስተኛ ነኝ።”

ምክንያታዊ የሆኑ ባለሥልጣናት ይህን መመሪያ በማውጣታቸው አመስጋኞች ነን፤ መመሪያው በኬንያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች በሃይማኖታዊ እምነታቸው ጸንተው መቆማቸውን እንዲቀጥሉ ያግዛቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:58