በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 5, 2023
ኬንያ

የኬንያ ፍርድ ቤት የተማሪዎችን የአምልኮ ነፃነት የሚያስከብር ውሳኔ አስተላለፈ

የኬንያ ፍርድ ቤት የተማሪዎችን የአምልኮ ነፃነት የሚያስከብር ውሳኔ አስተላለፈ

ግንቦት 12, 2023 የኬንያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ በአገሪቱ ያሉ ተማሪዎችን ሃይማኖታዊ ነፃነት የሚያስከብር ትልቅ ውሳኔ አስተላለፈ። የኬንያ ሕግ፣ ማንም ሰው ከሃይማኖታዊ እምነቱ ጋር በሚጋጭ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዲካፈል ሊገደድ እንደማይገባ ይገልጻል፤ ያም ሆኖ ከ2015 አንስቶ በአጠቃላይ 41 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች በሌሎች ሃይማኖቶች እንቅስቃሴ ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከትምህርት ቤት ተባረዋል።

ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ በ2017 ከተፈጸመ አንድ ክንውን ጋር የተያያዘ ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ዘጠኝ ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው በተካሄደ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ለመካፈል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ በአክብሮት ገለጹ። በዚህ አቋማቸው የተነሳም ክስ ተመሠረተባቸው። በ2019 አንድ የበታች ፍርድ ቤት፣ ትምህርት ቤቱ የይሖዋ ምሥክር የሆኑትን ልጆች በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ እንዲካፈሉ ማስገደዱ መሠረታዊ መብታቸውን የሚጥስ አይደለም የሚል ውሳኔ አስተላለፈ። ግንቦት 12, 2023 ግን የኬንያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ የበታች ፍርድ ቤቱ ውሳኔ “[የተማሪዎችን] የመማርና በክብር የመያዝ መብት የሚጥስ” እንደሆነ ገለጸ። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች በሌሎች ሃይማኖቶች እንቅስቃሴ እንዲካፈሉ የሚጠይቁ ሕጎች “አድልዎ የሚንጸባረቅባቸው፣ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረሩና ተፈጻሚ መሆን የማይችሉ ናቸው” አለ። በዚህ ችሎት ላይ የተሳተፉ አንድ ዳኛ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው፣ የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ መብቶች በተመለከተ ለትምህርት ቤቶች ለወደፊቱም መመሪያ ለመስጠት ነው።”

ይህ ውሳኔ መጋቢት 2022 የኬንያ የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን፣ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች የሁሉንም ተማሪዎች ሃይማኖታዊ መብቶች ሊያከብሩ እንደሚገባ የሚገልጽ መመሪያ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። በተጨማሪም ውሳኔው፣ ኬንያን የይሖዋ ምሥክር ተማሪዎችን መሠረታዊ መብቶች የሚያስከብሩ ተመሳሳይ ውሳኔዎችን ካስተላለፉ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ የአፍሪካ አገሮች ተርታ ያስመድባታል፤ ማላዊና ሩዋንዳም እንዲህ ያለ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

በኬንያም ሆነ በዓለም ዙሪያ ያሉ ደፋር ልጆች፣ ለንጹሕ አምልኮ ጠንካራ አቋም ለመያዝ በሚያደርጉት ጥረት ይሖዋ በጣም እንደሚኮራባቸው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ!—ምሳሌ 29:25