መስከረም 4, 2019
ኬንያ
የይሖዋ ምሥክሮች ኬንያ ውስጥ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን በሉኦ ቋንቋ አወጡ
ነሐሴ 30, 2019 በኪሱሙ፣ ኬንያ በተደረገ የክልል ስብሰባ ላይ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሉኦ ቋንቋ መውጣቱ ተገለጸ። የኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሬሚ ፕሪንግል በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ላይ መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን አብስሯል። ስብሰባው በቀጥታ በተላለፈባቸው ሁለት ሌሎች የስብሰባ ቦታዎች የተገኙትን ሰዎች ጨምሮ አጠቃላይ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 2,481 ነበር።
የትርጉም ሥራው ሦስት ዓመት ገደማ ወስዷል። የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሉኦ ቋንቋ የሚወጣበትን ጊዜ ሲናፍቁ የኖሩት ወንድሞችና እህቶች በእጅጉ እንደሚደሰቱ እርግጠኛ ነኝ። በጉባኤዎቻችን ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ቤተሰቦች ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት አቅማቸው አይፈቅድም፤ ስለዚህ እያንዳንዳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት መቻላቸው ትልቅ በረከት ነው። ደግሞም ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀመው ዘመናዊ ቋንቋ ስለሆነ ወንድሞች የሚያደርጉት የግልና የቤተሰብ ጥናት አስደሳችና እምነት የሚያጠናክር ይሆንላቸዋል።”
አዲስ ዓለም ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል በ184 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ ከእነዚህ መካከል በ2013 በወጣው እትም ላይ ተመሥርተው ተሻሽለው የወጡ 25 ቋንቋዎችም ይገኙበታል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ሥር ያሉትን የሉኦ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ 1,800 ገደማ አስፋፊዎች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን። በተጨማሪም ሉኦ ቋንቋ ለሚናገሩት ከ5 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስበክ ያስችላል።—ማቴዎስ 24:14