ግንቦት 30, 2023
ኮሎምቢያ
በኮሎምቢያ የሚገኘው የዋዩናይኪ የርቀት የትርጉም ቢሮ ቦታ ቀየረ
ሪዮአቻ፣ ኮሎምቢያ ውስጥ የተከፈተው አዲሱ የዋዩናይኪ ቋንቋ የርቀት የትርጉም ቢሮ መጋቢት 18, 2023 ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰነ። ዋዩናይኪ ቋንቋ 700,000 ተናጋሪዎች እንዳሉት ይገመታል፤ ኮሎምቢያና ቬኔዙዌላ ውስጥ ብዙ ተናጋሪዎች ያሉት የአገሬው ተወላጆች ቋንቋ ነው።
ከዚህ ቀደም የርቀት የትርጉም ቢሮው የሚሠራው በሁለት የኪራይ ቤቶች ውስጥ ሆኖ ነበር፤ ሆኖም የቦታ ማነስ፣ የኃይል መቆራረጥ እንዲሁም የስልክና የኢንተርኔት ችግር ነበረበት። በመሆኑም የኮሎምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ በመኖሪያ ሰፈር የሚገኙ ስድስት ቤቶችን ገዛ፤ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውሉም የማሻሻያ ሥራ ተደረገላቸው። እነዚህ ቤቶች በትርጉም ቢሮው ለሚሠሩ ወንድሞችና እህቶች መኖሪያና ቢሮ ሆነው ያገለግላሉ። ፕሮጀክቱ ጥቅምት 2022 ከጸደቀ በኋላ ጥር 2023 ተጠናቅቋል።
የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት አባል የሆነው ወንድም ህዋን ፌሊፔ ሮድሪጌስ አዲሱ ቦታ የተሻለ የሆነባቸውን አቅጣጫዎች ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “አዲሱ የትርጉም ቢሮ የተሻለ የቅጂ ስቱዲዮ የያዘ ነው፤ በቡድን ተገናኝቶ ለመሥራት አመቺ የሆነ ቦታ አለው፤ የተሻለ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ነው፤ እንዲሁም በተደጋጋሚ ለሚከሰተው የኃይል መቆራረጥ እልባት ለመስጠት ጄነሬተር ተገጥሞለታል።”
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ዋዩናይኪ ቋንቋ የመተርጎም ሥራ የተጀመረው በ1998 ነው። በአሁኑ ወቅት 14 ወንድሞችና እህቶች በዚህ ሥራ እያገዙ ነው። በዋዩናይኪ ቋንቋ በሚመሩ 20 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 400 ገደማ አስፋፊዎች አሉ።
የይሖዋ ድርጅት ከሁሉም ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎች ‘ወደ አምላክ እንዲቀርቡ’ ለመርዳት እያደረገ ያለውን ጥረት ማየት በእርግጥም አስደሳች ነው።—ያዕቆብ 4:8