ሰኔ 8, 2021
ኮሎምቢያ
በኮሎምቢያ የተካሄደ የእርዳታ ሥራ
ከሚያዝያ 2021 መጨረሻ አንስቶ ኮሎምቢያ በሕዝባዊ ዓመፅ ስትታመስ ቆይታለች። በዓመፁ የሞተ ወይም የቆሰለ አንድም የይሖዋ ምሥክር የለም። ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች ምግብና ነዳጅ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። ወንድሞቻችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተጨማሪ በቅርቡ የተከሰተው የመሠረታዊ ነገሮች እጥረት ከባድ ችግር አድርሶባቸዋል።
የኮሎምቢያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለመርዳት ሲል አምስት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። እነዚህ ኮሚቴዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የወጡትን የደህንነት ደንቦች በጠበቀ መልኩ የእርዳታ ሥራውን እያከናወኑ ነው። ወንድሞችና እህቶች በተለይ ከምግብ ጋር በተያያዘ እርስ በርስ እየተረዳዱ ነው። የጉባኤ ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ደግሞ ለአስፋፊዎች መንፈሳዊ እርዳታ እያደረጉ ነው።
በአንዱ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለው ወንድም አልሞንድ ዊንክላር እንዲህ ብሏል፦ “ያጋጠመን ሁኔታ በጣም ከባድ ነው። ይሖዋ በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ለሕዝቡ ቶሎ በመድረሱ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”
በላ ሎሞ አሪና ጉባኤ የሚገኙ 18 አስፋፊዎችና ቤተሰቦቻቸው የምግብ እርዳታ ደርሷቸዋል። በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንድ አቅኚ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል፦ “የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው የሚያስፈልገንን እርዳታ ሲያቀርብልን ደስታችን ወሰን አልነበረውም። እርዳታው የጸሎታችን መልስ እንደሆነ ይሰማናል። መንፈሳዊ ቤተሰባችን ልክ የሚያስፈልገንን ነገር ስላቀረበልን እንዲሁም ይሖዋ ብርታትና ጽናት ስለሰጠን በጣም አመስጋኝ ነን።”
የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ፣ ብዙዎቹን ቁሳቁሶች የገዙት ከአንድ ትልቅ ሱፐር ማርኬት ነበር፤ በዚያ የሚሠሩ ሠራተኞች ለእርዳታ ሥራው ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጸዋል። አንዱ ሠራተኛ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሰዎች ቤት እየሄዱ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያስተምሩ አውቅ ነበር፤ ግን የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ያከናወኑትን ግሩም ሥራ ሳይ በጣም ተደንቄያለሁ።”
ወንድሞቻችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላቸውን አላቆሙም። ውድ ወንድሞቻችን ‘የዓለም ክፍል ላለመሆን’ ጥረት ሲያደርጉ ይሖዋ እነሱን በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ መንከባከቡን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—ዮሐንስ 17:16