ሰኔ 9, 2023
ኮሎምቢያ
በጉዋምቢያኖ እና በኤምቤራ (ቻሚ) ቋንቋዎች እስከ ዛሬ ተደርጎ የማያውቅ ስብሰባ ተካሄደ
እሁድ መጋቢት 26, 2023 ካሊ፣ ኮሎምቢያ ውስጥ ብዙ ቋንቋዎችን ያስተናገደ በዓይነቱ ልዩ ፕሮግራም ተካሂዷል። የስፓንኛ የወረዳ ስብሰባ፣ ጉዋምቢያኖ እና ኤምቤራ (ቻሚ) በተባሉት የአገሬው ነባር ሕዝቦች ቋንቋዎች በቀጥታ እየተተረጎመ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው ነው። በስብሰባው ላይ ከ1,600 በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። ከእነዚህ መካከል 48ቱ ጉዋምቢያኖ ተናጋሪዎች ሲሆኑ 78ቱ ደግሞ ኤምቤራ (ቻሚ) ተናጋሪዎች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ኮሎምቢያ ውስጥ ከ21,000 በላይ ጉዋምቢያኖ ተናጋሪዎች እንዲሁም ከ77,000 በላይ ኤምቤራ (ቻሚ) ተናጋሪዎች አሉ። ከዚህ ቀደም ኮሎምቢያ ያሉት የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሾች፣ ፕሮግራሞች ወደ ሌላ ቋንቋ በቀጥታ እየተተረጎሙ እንዲካሄዱ የሚያስችሉ መሣሪያዎች አልነበሯቸውም። በመሆኑም ከአገሬው ነባር ሕዝቦች የመጡ ተሰብሳቢዎች በደንብ በማይረዱት የስፓንኛ ቋንቋ በሚካሄድ የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ይገደዱ ነበር።
የአገሬው ነባር ሕዝቦች አባላት የሆኑ ቤተሰቦች ስለ አሁኑ የወረዳ ስብሰባ ሲሰሙ ወዲያውኑ ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ማጠራቀም ጀመሩ። ካራስኮና የቤተሰቡ አባላት ያደረጉትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ስምንት አባላት ያሉት ይህ ቤተሰብ የሚኖረው ገጠር ነው። የወረዳ ስብሰባው ወደሚካሄድበት አዳራሽ ለመሄድ 3 ሰዓት በእግር መጓዝ፣ ከዚያም ለ12 ሰዓታት በአውቶብስ መሄድ ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና የቦታው ርቀትም ሆነ የሚጠይቀው ወጪ ቅንዓታቸውን አላቀዘቀዘውም። ዝግጅት ማድረግ የጀመሩት ከወራት በፊት ነው፤ ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን ባሕላዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶች እየሠሩ መሸጥ ጀመሩ። በወረዳ ስብሰባው ላይ ከተጠመቁት ሁለት የኤምቤራ (ቻሚ) ተናጋሪ አስፋፊዎች አንዱ የዚህ ቤተሰብ የ12 ዓመት ልጅ ነው። ጉዋምቢያኖ ተናጋሪ የሆኑ ሁለት አስፋፊዎችም በስብሰባው ላይ ተጠምቀዋል።
በወረዳ ስብሰባው ላይ የጉዋምቢያኖ አስተርጓሚ የነበረች አድሪያኒን ሞራሌስ የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የወረዳ ስብሰባው በቋንቋዬ መተርጎሙ በጣም ደስ ብሎኛል። ስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ የይሖዋን መልእክት በገዛ ቋንቋቸው እንደሚሰሙ ማወቄ ልቤን ነክቶታል።”
ወንድም ዲዮሜዴስ ቬላስኮ የተባለ ሌላ የጉዋምቢያኖ አስተርጓሚ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “የማስተርጎም ኃላፊነት እንደተሰጠኝ ሲነገረኝ መጀመሪያ ላይ ፈርቼ ነበር። ይሁንና ይሖዋ ለአገሬው ነባር ሕዝቦች እያደረጋቸው ያሉትን ድንቅ ነገሮች ስመለከት ድፍረት አገኘሁ። ይሖዋ የሰጠኝን ይህን ኃላፊነት መቀበሌ ትልቅ መብት እንደሆነ ተሰማኝ።”
ከሁሉም ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች “ኑ፤ ወደ ይሖዋ ተራራ . . . እንውጣ” ሲሉ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ኢሳይያስ 2:3