በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ ወንድም ናታን ኖር እና ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ በ1946 በቦጎታ ያሉ ወንድሞችና እህቶችን ሲጎበኙ። በስተ ቀኝ፦ በኮሎምቢያ የነበሩ ሚስዮናውያን (ከላይ፣ ከግራ ወደ ቀኝ) ኦላፍ ኦልሰን፣ ጄምስ ዌብስተር፣ ኩዊን ዴል ሎደርዴል፤ (ከታች፣ ከግራ ወደ ቀኝ) አን ሎደርዴል፣ ሄለን ላንግፎርድ እና ጁወል ሃርፐር

ሚያዝያ 12, 2022
ኮሎምቢያ

የኮሎምቢያ የ100 ዓመት ቲኦክራሲያዊ ታሪክ

የኮሎምቢያ የ100 ዓመት ቲኦክራሲያዊ ታሪክ

የይሖዋ ምሥክሮች በኮሎምቢያ ሥራቸውን ማከናወን ከጀመሩ 100 ዓመት የሞላቸው በ2022 ነው። a

ሄሊዮዶሮ ኸርናንዴዝ

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚወደው ሄሊዮዶሮ ኸርናንዴዝ በ1922 የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ ጓደኛው በርካታ መጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን ተዋሰ። ሄሊዮዶሮ እውነትን እንዳገኘ ወዲያውኑ ስለተገነዘበ መልእክቱን ለሌሎች መናገር ጀመረ። ለሁለት ዓመታት ሲሰብክ ከቆየ በኋላ ሁዋን ኤስቱፒናን የተባለ ሰው አገኘ፤ እሱም አብሮት ምሥራቹን መስበክ ጀመረ። ሁለቱም በ1932 ተጠመቁ።

ሁዋን ኤስቱፒናን

ከጊዜ በኋላ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለወንድም ኸርናንዴዝና ለወንድም ኤስቱፒናን በባትሪ የሚሠራ የድምፅ ማጫወቻ መሣሪያ ላከላቸው። ወንድሞች “ሥላሴ ተጋለጠ” እንዲሁም “የዓለም መጨረሻ” እንደሚሉት ያሉ መንፈሳዊ ንግግሮችን በአንዲስ ተራሮች ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ያጫውቱ ነበር። እነዚህ አካባቢዎች በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ ሥር ስለነበሩ ወንድሞች ብዙ ጊዜ ተቃውሞ ያጋጥማቸው ነበር።

በ1945 በጊልያድ የሠለጠኑ ሚስዮናውያን ወደ አገሪቱ መጡ። ከእነዚህ ሚስዮናውያን አንዱ የሆነው ወንድም ኦላፍ ኦልሰን ከጊዜ በኋላ በሕይወት ታሪኩ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “እዚህ በርካታ የይሖዋ በጎች አሉ፤ ይሖዋ እነሱን በመፈለጉና በመመገቡ ሥራ እንድንካፈል ስለላከን አመስጋኞች ነን።”

ሥራውን ይበልጥ ለማደራጀት በኮሎምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ፤ ቅርንጫፍ ቢሮው ግንቦት 1, 1946 ሥራ ጀመረ። የመጀመሪያው የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ የሆነው ወንድም አርተር ግሪን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በይሖዋ ኃያል መንፈስ እርዳታ እውነተኛው አምልኮ በኮሎምቢያ እየተቋቋመ ነው።”

በዛሬው ጊዜ ኮሎምቢያ ውስጥ ምሥራቹን በቅንዓት የሚሰብኩ 190,000 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ።

ኮሎምቢያ የምትታወቀው ባላት ለም አፈርና ዕፁብ ድንቅ በሆኑት የከበሩ ድንጋዮቿ ነው። ሆኖም ኮሎምቢያን ይበልጥ ውብ ያደረጓት፣ ይሖዋ ወደ ራሱ እየሳባቸው ያሉት “የከበሩ ነገሮች” ናቸው። ይሖዋ ‘ቤቱን በክብር የሚሞላውን’ የስብከቱን ሥራ እየባረከው መሆኑን በማየታችን ደስተኞች ነን።—ሐጌ 2:7

a የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም መጠቀም የጀመሩት በ1931 ነው።