ግንቦት 14, 2024
ኮት ዲቩዋር
በኮት ዲቩዋር በተካሄደ የእግር ኳስ ውድድር ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አሰራጩ
ከጥር 13 እስከ የካቲት 11, 2024 መላውን አፍሪካ ያሳተፈው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተካሂዶ ነበር። የውድድሩ አስተናጋጅ አገር ኮት ዲቩዋር ስትሆን ከ24 አገራት የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ውድድሩን ታድመዋል። በውድድሩ ወቅት፣ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለእንግዶቹ ለማካፈል የስብከት ዘመቻ አድርገዋል። ውድድሩ በተካሄደባቸው አምስት ትላልቅ ከተሞች ላይ ከ120 በላይ የጽሑፍ ጋሪዎችን አቁመዋል።
አቢጃን ከተማ ውስጥ አንድ ወጣት ወደ ጽሑፍ ጋሪያችን ቀረብ አለና የምትወዱት ሰው ሲሞት የሚለውን ብሮሹር መውሰድ ፈለገ። የሚወደው ጓደኛው በቅርቡ እንደሞተ ለወንድሞች ነገራቸው። ወንድሞች ዮሐንስ 5:28, 29 ላይ የሚገኘውን የሚያጽናና ጥቅስ ሲያነብቡለት ወጣቱ ልቡ ተነካ። ውይይቱን መቀጠል ስለሚፈልግ ቤቱ መጥተው እንዲያናግሩት ወንድሞችን ጋበዛቸው።
በሌላ ጊዜ ደግሞ በአንያማ አንድ የፖሊስ ኮሚሽነር ወደ ጽሑፍ ጋሪያችን መጣ። ጽሑፎቻችንን በተለይ ደግሞ ስለ ፍጥረትና ስለ ሕይወት አመጣጥ የሚናገሩትን ጽሑፎች ማንበብ እንደሚወድ ለወንድሞች ነገራቸው። ምንም እንኳ ሥራ እንደሚበዛበት ቢገልጽም ወንድሞች ደውለው እንዲያነጋግሩት ስልክ ቁጥሩን ሰጣቸው።
አቢጃን ከተማ ውስጥ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ሰው ወደ ጋሪው መጣ፤ ወጣት ሳለ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠና እንደነበረና በኋላ ላይ ከጉባኤው ጋር እንደተጠፋፋ ገለጸ። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖቶች በጣም እንደሚለዩ አስተዋለ። በተለይ ደግሞ የፖለቲካ አለመረጋጋት በሚከሰትበት ወቅት በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚታየው ሰላምና አንድነት አስገረመው። ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወንድሞች በቋሚነት እያስጠኑት ነው።
የኮት ዲቩዋር ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” እንዲሰሙ ለመርዳት የሚያስችል እንዲህ ያለ ግሩም አጋጣሚ በማግኘታቸው እኛም ተደስተናል።—የሐዋርያት ሥራ 2:11