ሰኔ 24, 2020
ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ
በኮንጎ (ኪንሻሳ) ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ያሉ ወንድሞች ወረርሽኝ፣ ጎርፍና የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለባቸውን ችግር በጽናት እየተወጡ ነው
በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክና በኮንጎ ሪፑብሊክ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጨማሪ ጎርፍና የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን መዘዝ እየተጋፈጡ ነው። በእነዚህ ሁለት አገሮች የሚከናወነውን የስብከት ሥራ በበላይነት የሚከታተለው የኮንጎ (ኪንሻሳ) ቅርንጫፍ ቢሮ ለእነዚህ ወንድሞች ቁሳዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጅት አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ ቅርንጫፍ ቢሮው፣ በዚያ ክልል ውስጥ ላሉ ወንድሞች እርዳታ የሚሰጡ 57 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። እስካሁን ድረስ በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ከ90,000 ለሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ምግብ ማቅረብ ተችሏል።
ሚያዝያ 16 እና 17, 2020 በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ምሥራቃዊ ግዛቶች ላይ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ጎርፍ ያስከተለ ሲሆን በዚህም ምክንያት 139 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። እነዚህ አስፋፊዎች በወንድሞችና በእህቶች ቤት ተጠልለዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ያሉት የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉት ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ መጠለያ ለማዘጋጀት ጥረት እያደረጉ ነው።
ወንድሞችና እህቶች የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ በልግስና መዋጮ እያደረጉ ነው። በአንድ አካባቢ አስፋፊዎች 700 ኪሎ ግራም ሙዝ፣ 400 ኪሎ ግራም በቆሎ እንዲሁም 220 ኪሎ ግራም ካሳቫና የካሳቫ ቅጠሎች አሰባስበዋል።
በተጨማሪም ሳም 26 ኬኤም ተብሎ በሚጠራው ጉባኤ ውስጥ ያሉት 60 አስፋፊዎች በእርስ በርስ ጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ 50 ወንድሞችን ተቀብለዋል። አስፋፊዎቹ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ እርዳታ እስኪደርሳቸው ድረስ፣ ያላቸውን ምግብ ከተፈናቀሉት ወንድሞች ጋር ተካፍለው ተመግበዋል።
የኮንጎ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በብራዛቪል የሚኖር አንድ የቤተሰብ ራስ እርዳታ ከተደረገለት በኋላ የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወት በቅጽበት ሊለወጥ ይችላል። እኔ ሠርቼ የማገኘው መጠነኛ ደሞዝና ባለቤቴ አንዳንድ ተባራሪ ሥራዎችን ሠርታ የምታገኘው ገንዘብ አንድ ላይ ተደምሮ ወጪያችንን ለመሸፈን ያስችለን ነበር። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት ግን የገቢ ምንጫችን ሁሉ ነጠፈ። ያም ሆኖ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት አላጣንም። በእጃችን ላይ ያለው ነገር ሁሉ ሲያልቅ ምን እንደምናደርግ እየተነጋገርን ባለንበት ሰዓት ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ ረዳን።”
በኪንሻሳ ከተማ የምትኖር ባሏን በሞት ያጣች ምቡዪ ኤስተር የተባለች እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴን በሞት ያጣሁት ከአንድ ወር በፊት ነው። ምንም የገቢ ምንጭ ስላልነበረኝ ሦስት ልጆቼን ለመመገብ እቸገር ነበር። ቤተሰባችን ለዚህ ሁሉ ቀን የሚበቃ እንዲህ ያለ ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ ማግኘት የሚችልበት ምንም መንገድ አልነበረም። ይሖዋ፣ በጣም እናመሰግናለን!”
ይሖዋ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መንከባከቡን እንዲቀጥልና የእርዳታ ሥራውን እንዲባርክ እንጸልያለን። በተጨማሪም ሁሉም ሰው ምድር ከምታቀርበው የተትረፈረፈ ምርት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን።—መዝሙር 72:16