ጥር 2, 2020
ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ
ኮንጎ በጎርፍ ተጥለቀለቀች
በማዕከላዊ አፍሪካ የምትገኘው ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ በኃይለኛ ዝናብና በጎርፍ የተነሳ አደገኛ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። የኮንጎ (ኪንሻሳ) ቅርንጫፍ ቢሮ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በጎርፍ መጥለቅለቁ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዘግቧል። የሚያሳዝነው በዋና ከተማዋ በኪንሻሳ ውስጥ የአንድ ወንድማችን ሕይወት በጎርፉ የተነሳ አልፏል።
የኮንጎ (ኪንሻሳ) ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ሪፖርት ልኳል፦
በደቡብ ምዕራብ ኮንጎ በሚገኘው በካሳይ ግዛት የደረሰው ኃይለኛ ነፋስና ከባድ ዝናብ የስድስት ቤተሰቦችን ቤቶች አውድሟል።
በሰሜን ምዕራብ ኮንጎ በሚገኘው በሱድ ኡባንጊ ግዛት አንድ የስብሰባ አዳራሽ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ተጥለቅልቋል። አዳራሹን የሚጠቀሙት በድምሩ 69 አስፋፊ ያላቸው ሦስት ጉባኤዎች ነበሩ። በአካባቢው የሚኖሩ 22 ቤተሰቦችም በጎርፍ መጥለቅለቁ ተጎድተዋል። ቅርንጫፍ ቢሮው በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች ቁሳዊና መንፈሳዊ እርዳታ የመስጠቱን ሥራ እንዲያደራጁ አንድ ልዩ አቅኚና አንድ ሌላ ሽማግሌ መድቧል።
በትሾፖ ግዛት ውስጥ በኮንጎ ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ከቤታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። በተጨማሪም በአካባቢው ካሉ የስብሰባ አዳራሾች መካከል ቢያንስ አንዱ በጎርፍ ተጥለቅልቋል።
በዋና ከተማዋ በኪንሻሳ ያሉ ጉባኤዎች ቢያንስ 80 ቤተሰቦች በጎርፍ መጥለቅለቁ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገዋል።
የጎርፍ መጥለቅለቁ በአገሪቱ ያስከተለው ቆሻሻና ብክለት ለተለያዩ በሽታዎች ሊያጋልጥ ስለሚችል ቅርንጫፍ ቢሮው ጤንነትን መጠበቅ ስለሚቻልበት መንገድ ለአስፋፊዎቹ መረጃ እየሰጠ ነው።
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም ለእምነት አጋሮቻቸው ምግብና ልብስ በመስጠት እርስ በርስ እየተረዳዱ ነው። ከዚህም ሌላ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች በቅርንጫፍ ቢሮው አመራር ሥር ሆነው በእርዳታ ሥራው እየተካፈሉ ነው።
ሁላችንም የምናቀርበው ጸሎት እንዲሁም የይሖዋ ድርጅት የሚያበረክተው ቁሳዊና መንፈሳዊ እርዳታ በዚህ አስጨናቂ ዘመን ‘የሚያለቅሱትን ሁሉ እንደሚያጽናናቸው’ እንተማመናለን።—ኢሳይያስ 61:1, 2