በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 28, 2023
ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በሊንጋላ ቋንቋ እንዲሁም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በስድስት ቋንቋዎች ወጡ

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በሊንጋላ ቋንቋ እንዲሁም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በስድስት ቋንቋዎች ወጡ

ማክሰኞ ነሐሴ 29, 2023 የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በሊንጋላ ቋንቋ ወጣ። በተጨማሪም በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አሉር፣ ኡሩንድ፣ ኪሶንጌ፣ ኪቱባ፣ ኪናንዴ እና ኪፔንዴ በተባሉት ቋንቋዎች ወጥተዋል። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን በኪንሻሳ፣ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ማርተርስ ስታዲየም በተካሄደው “በትዕግሥት ጠብቁ”! በተባለው የክልል ስብሰባ ላይ ለተገኙት 75,715 ሰዎች ንግግር አቅርቧል። ሌሎች 219,457 ሰዎች በ53 የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሾችና በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ በሆኑ ሌሎች ቦታዎች ሆነው ንግግሩን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታትለዋል። በሊንጋላ ቋንቋ የተዘጋጀው የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም እና በኪሶንጌ ቋንቋ የተዘጋጀው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የታተሙ ቅጂዎች በስብሰባው ላይ ለተገኙት ሰዎች ተሰራጭተዋል። በሌሎቹ ቋንቋዎች የተዘጋጁት ትርጉሞች የታተሙ ቅጂዎች ወደፊት ይወጣሉ። የሁሉም ትርጉሞች ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች ወዲያውኑ ተለቅቀዋል። የወጡት ትርጉሞች ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፦

አሉር (ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፦ ከዘፍጥረት እስከ ኢዮብ፣ መኃልየ መኃልይ)

  • ወደ 1,750,000 የሚጠጉ ሰዎች የአሉር ቋንቋ የሚናገሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ የቋንቋው ተናጋሪዎች የሚኖሩት ማሃጊ ውስጥ ነው

  • 1,609 አስፋፊዎች በአሉር ቋንቋ በሚመሩ 45 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ

  • የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ወደ አሉር ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ2013 ነው

  • የርቀት የትርጉም ቢሮው የሚገኘው ቡኒያ ውስጥ ነው

ኪናንዴ (የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት)

  • በኢቱሪና በሰሜን ኪቩ የሚኖሩ 903,000 ገደማ ሰዎች የኪናንዴ ቋንቋ ይናገራሉ

  • 4,793 አስፋፊዎች በኪናንዴ ቋንቋ በሚመሩ 78 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ

  • የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ወደ ኪናንዴ ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ1998 ነው

  • የርቀት የትርጉም ቢሮው የሚገኘው ቡቴምቦ ውስጥ ነው

ኪፔንዴ (ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፦ ዘፍጥረት፣ ዘፀአት፣ ዘሌዋውያን፣ መሳፍንት፣ ሩት፣ አንደኛና ሁለተኛ ሳሙኤል እና መኃልየ መኃልይ)

  • በካሳይ፣ በክዊሉ እና በክዋንጎ ክልሎች የሚኖሩ 2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ኪፔንዴ ቋንቋ እንደሚናገሩ ይገመታል

  • 3,349 አስፋፊዎች በኪፔንዴ ቋንቋ በሚመሩ 88 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ

  • የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ወደ ኪፔንዴ ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ1996 ነው

  • የርቀት የትርጉም ቢሮው የሚገኘው ኪክዊት ውስጥ ነው

ኪሶንጌ (ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፦ ዘፍጥረት፣ ዘፀአት እና መኃልየ መኃልይ። እንዲሁም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት)

  • ኪሶንጌ ቋንቋ የሚናገሩ 1 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ያሉ ሲሆን አብዛኞቹ የሚኖሩት ሎማሚ ክልል ውስጥ ነው

  • 1,043 አስፋፊዎች በኪሶንጌ ቋንቋ በሚመሩ 31 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ

  • የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ወደ ኪሶንጌ ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ2006 ነው

  • የትርጉም ቢሮው የሚገኘው ኪንሻሳ ውስጥ ነው

ኪቱባ (ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፦ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሮም፣ አንደኛና ሁለተኛ ቆሮንቶስ፣ ገላትያ እና ፊልጵስዩስ)

  • በኮንጎ ሪፑብሊክ ደቡባዊ ክፍል፣ በአንጎላ እና በጋቦን የሚኖሩ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኪቱባ ቋንቋ ይናገራሉ

  • 2,137 አስፋፊዎች በኪቱባ ቋንቋ በሚመሩ 30 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ

  • የኪቱባ ቋንቋ የርቀት የትርጉም ቢሮ የተከፈተው በ2019 ሲሆን የሚገኘው በፖንት-ኖር ነው

ሊንጋላ (የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም)

  • ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሊንጋላ ቋንቋ ይናገራሉ

  • 74,023 አስፋፊዎች በሊንጋላ ቋንቋ በሚመሩ 1,266 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ

  • የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ወደ ሊንጋላ ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ1960ዎቹ ነው

  • አዲስ ዓለም ትርጉም በሊንጋላ ቋንቋ የወጣው በ2009 ነበር

  • የትርጉም ቢሮው የሚገኘው ኪንሻሳ ውስጥ ነው

ኡሩንድ (ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፦ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሮም እና አንደኛ ቆሮንቶስ)

  • 153,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ኡሩንድ የሚናገሩ ሲሆን አብዛኞቹ የሚኖሩት ሉዋላባ ውስጥ ነው

  • 553 አስፋፊዎች በኡሩንድ ቋንቋ በሚመሩ 19 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ

  • የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ወደ ኡሩንድ ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ1994 ነው

  • የርቀት የትርጉም ቢሮው የሚገኘው ኮልዌዚ ውስጥ ነው

እነዚህ አዲስና የተሻሻሉ ትርጉሞች ቋንቋዎቹ በሚነገሩባቸው መስኮች ላይ የሚያገለግሉትን ወንድሞችና እህቶች በእጅጉ ይጠቅሟቸዋል። አንድ የኪቱባ ቋንቋ ተናጋሪ አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “በክልሉ ውስጥ ያሉት ሰዎች ስናነጋግራቸው በቋንቋቸው በተዘጋጁ ጽሑፎች ስለማንጠቀም ብዙውን ጊዜ መልእክታችንን እንደማይሰሙ አስተውለን ነበር። ለምሳሌ ጥቅሶችን በፈረንሳይኛ ስናነብላቸው መልእክቱ አይገባቸውም። ይህን አዲስ ትርጉም ግን በደንብ ማንበብ የማይችሉ ሰዎች እንኳ ሲነበብላቸው ይረዱታል፤ ከአምላክ ቃልም ጥቅም ያገኛሉ።” ሊንጋላ ተናጋሪ የሆነ አስፋፊ የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም የሚያስገኘውን ጥቅም ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለ ቀላል ቋንቋ የሚጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘት በአገልግሎት ላይ ለሌሎች ልናካፍለው የምንችለው ውድ ሀብት እንደማግኘት ነው።”

በኪንሻሳ በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ 75,715 ሰዎች ተገኝተዋል

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እነዚህን አዳዲስ ትርጉሞች በመጠቀም፣ “የአምላክን ቃል ለመስማት [የሚጓጉ]” ሰዎችን ልብ ለመንካት የሚያደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርከው ጽኑ እምነት አለን።​—የሐዋርያት ሥራ 13:7