ነሐሴ 5, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና
ሐምሌ 2024 በዓለም ዙሪያ አሥር መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ
ማላዊ ምልክት ቋንቋ
የማላዊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኮሊን ካርሰን ሐምሌ 5, 2024 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በማላዊ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። ይህን ዜና ያበሰረው በሊሎንግዌ፣ ማላዊ በተደረገው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተባለው የ2024 የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ ነው፤ በስብሰባው ላይ 331 ሰዎች ተገኝተው ነበር። የኤሌክትሮኒክ ቅጂውን ወዲያውኑ jw.org እና JW ላይብረሪ ምልክት ቋንቋ አፕሊኬሽን ላይ ማግኘት ተችሏል።
ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ማላዊ ምልክት ቋንቋ የተተረጎመው የመጀመሪያው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ሲሆን ከ400,000 የሚበልጡ ሰዎች ይህን ቋንቋ ይጠቀማሉ። በአሁኑ ጊዜ ማላዊ ውስጥ በ16 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና በስምንት ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ600 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አሉ።
ሲቤምባ
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌጅ ፍሊግል የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሲቤምባ ቋንቋ መውጣቱን ሐምሌ 19, 2024 አበሰረ። ይህን ዜና ያበሰረው በንዶላ፣ ዛምቢያ በሚገኘው በሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተባለው የ2024 የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ ነው። በአጠቃላይ 23,336 ሰዎች በስብሰባው ላይ በአካል ተገኝተዋል። ተጨማሪ 5,920 ሰዎች ደግሞ ከአምስት የተለያዩ የትላልቅ ስብሰባ ቦታዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። በስድስቱም የስብሰባ ቦታዎች የተገኙ ሁሉ የአዲስ ዓለም ትርጉም የታተመ ቅጂ ደርሷቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱሱን የኤሌክትሮኒክ ቅጂም ሆነ የሩት፣ የ1 ዮሐንስ፣ የ2 ዮሐንስ እና የ3 ዮሐንስ መጻሕፍትን የድምፅ ቅጂዎች ወዲያውኑ ማውረድ ተችሏል።
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ላይ በሲቤምባ ቋንቋ የወጣው በ2008 ነበር። ዛምቢያ ውስጥ የሲቤምባ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወደ አራት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ ይታመናል፤ ከእነዚህ መካከል በአገሪቱ ዙሪያ ባሉ 1,856 ጉባኤዎችና 8 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 131,351 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይገኙበታል።
ኪቼ
የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሆሴ ቶሬስ ሐምሌ 19, 2024 መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በኪቼ ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። ይህ ማስታወቂያ የተነገረው በሳን ሉካስ ሳካቴፔኬስ፣ ጓቴማላ በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ በተባለው የ2024 የክልል ስበስባ ላይ ነው። በስብሰባው ላይ የተገኙት 405 ተሰብሳቢዎች በሙሉ የመጽሐፉን የታተመ ቅጂ አግኝተዋል። በተጨማሪም መጽሐፉን ወዲያውኑ jw.org እና JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ማግኘት ተችሏል።
የኪቼ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች እንዳሉ ይገመታል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የሚኖሩት በኪቼ ቋንቋ የሚካሄድ የመጀመሪያው ጉባኤ በተቋቋመበት በጓቴማላ ነው፤ ይህ ጉባኤ የተቋቋመው በ2010 ነበር። በአሁኑ ጊዜ በመላው አገሪቱ በ16 ጉባኤዎች የሚያገለግሉ 387 ወንድሞችና እህቶች አሉ።
ሹዋቡ/ማኩዋ ሜቶ/ማኩዋ ሺሪማ/ንሴንጋ (ሞዛምቢክ)/ፒምቢ/ቴዌ/ስዋ
ሐምሌ 28, 2024 በማፑቶ፣ ሞዛምቢክ በሚገኘው ኤስታዲዮ ናስዮናል ዶ ዚምፔቶ ልዩ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በአጠቃላይ 26,025 የሚሆኑ ሰዎች በስብሰባው ላይ በአካል ተገኝተዋል። ተጨማሪ 64,570 ሰዎች ደግሞ ከ16 የተለያዩ ቦታዎች ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተከታትለዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ ወንድም ፍሊግል በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መውጣታቸውን አብስሯል፤ የመጽሐፍ ቅዱሶቹን የታተመም ሆነ ኤሌክትሮኒክ ቅጂ ወዲያውኑ ማግኘት ተችሏል። ወንድም ፍሊግል መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በማኩዋ ሜቶ፣ በማኩዋ ሺሪማ እና በንሴንጋ (ሞዛምቢክ) ቋንቋዎች፣ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በሹዋቡ፣ በፒምቢ እና በቴዌ፣ ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በስዋ ቋንቋ መውጣቱን አስታውቋል።
እነዚህ ትርጉሞች ሲጨመሩ አዲስ ዓለም ትርጉም በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በ300 ቋንቋዎች ይገኛል!