ኅዳር 7, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና
መጠበቂያ ግንብ በፖርቱጋልኛ መዘጋጀት ከጀመረ አንድ ምዕተ ዓመት ተቆጠረ
በ1923 ወንድም ጆርጅ ያንግ፣ ቅርንጫፍ ቢሮ ለማቋቋምና የስብከቱን ሥራ ለማደራጀት ወደ ብራዚል ሄደ። እሱ በሄደበት ጊዜ በአገሪቱ ማግኘት የሚቻለው መጠበቂያ ግንብ እና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ (አሁን የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ በመባል ይታወቃል) የተባለውን መጽሔት የእንግሊዝኛ እትም ብቻ ነበር። ወንድም ጆርጅ መጠበቂያ ግንብ ወደ ፖርቱጋልኛ እንዲተረጎምና መጽሔቱ በአገሪቱ ባለ ማተሚያ ቤት እንዲታተም ወዲያውኑ ዝግጅት አደረገ። በውጤቱም ጥቅምት 1923 የመጀመሪያው ፖርቱጋልኛ የመጠበቂያ ግንብ እትም ወጣ። ከሦስት ዓመት በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ካለው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሕትመት ማሽን ተላከለት፤ በመሆኑም ወንድሞች መጽሔቶቹን ራሳቸው ማተም ጀመሩ።
በ1925 ማለትም በብራዚል የመጀመሪያው ፖርቱጋልኛ የመጠበቂያ ግንብ እትም ከወጣ ከሁለት ዓመት በኋላ በፖርቱጋል ያሉ ወንድሞች መጽሔቱን ወደ አውሮፓ ፖርቱጋልኛ መተርጎም ጀመሩ። ሆኖም በ1933 አምባገነን የሆነ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲወጣ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከፍተኛ ስደት ይደርስባቸው ጀመር። ብዙም ሳይቆይ በፖርቱጋል የሚካሄደው የትርጉም ሥራ ተቋረጠ። ከዚያ በኋላ ባሉት አሥርተ ዓመታት በፖርቱጋል ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ማግኘት የሚችሉት በብራዚል የሚዘጋጀውን ፖርቱጋልኛ መጠበቂያ ግንብ ብቻ ነበር። በወቅቱ በፖርቱጋል ትኖር የነበረች ኢዛቤል የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በሰዋስው ልዩነቶች እንዲሁም ቃላቱ በተናጠል በሚያስተላልፉት ትርጉም ላይ ከማተኮር ይልቅ አእምሮዬና ልቤ በመልእክቱ ላይ እንዲያተኩር አደረግኩ። በፖርቱጋል ያለን ወንድሞችና እህቶች መጠበቂያ ግንብ በቋንቋችን ማግኘት ባልቻልንበት ጊዜ በብራዚል ያሉ ወንድሞቻችን ጽሑፉን ያዘጋጁልን ስለነበር በጣም አመስጋኝ ነኝ።”
በ1961 የአዲስ ዓለም ትርጉም እንግሊዝኛ እትም አንድ ጥራዝ ሆኖ ሲወጣ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ፖርቱጋልኛን ጨምሮ ወደ ሌሎች ስድስት ቋንቋዎች እንዲተረጎም ፈቃድ ተሰጠ። ፈታኝ ቢሆንም በብራዚል ያለው የፖርቱጋልኛ ትርጉም ቡድን በሁሉም ፖርቱጋልኛ ተናጋሪ አገሮች ያሉ ሰዎች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ ቃላትን የመጠቀም ግብ ይዞ ተነሳ። ለብዙ ዓመታት መጠበቂያ ግንብ ወደ ፖርቱጋልኛ የሚተረጎመውም ይህንኑ መርሕ በመከተል ነበር። ሆኖም በ2017 መጠበቂያ ግንብ ወደ ፖርቱጋልኛ (ብራዚል) እንዲሁም ወደ ፖርቱጋልኛ (ፖርቱጋል) እንዲተረጎም ፈቃድ ተሰጠ።
በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ያሉ 1.2 ሚሊዮን ገደማ ፖርቱጋልኛ ተናጋሪ አስፋፊዎች እንዲሁም 260 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ፖርቱጋልኛ ተናጋሪ ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ ከሚዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ እትም መጠቀም ይችላሉ። እነዚህ ሰዎችም ሆኑ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች ብዙ ሰዎች “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” መማራቸውን እንዲቀጥሉ እንጸልያለን።—የሐዋርያት ሥራ 2:11