በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በጀርመን የተካሄደው የእርዳታ ሥራ (ከላይ በስተ ግራ)፣ በቤልጅየም የደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ (ከላይ በስተ ቀኝ)፣ በኔዘርላንድስ የደረሰው ውድመት (ከታች)

ሐምሌ 27, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ምዕራብ አውሮፓ በከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተመታ

ምዕራብ አውሮፓ በከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተመታ

ለበርካታ ቀናት፣ በተለይም ከሐምሌ 13 እስከ 17, 2021 የጣለው ኃይለኛ ዝናብ በቤልጅየም፣ በጀርመን፣ በሉክሰምበርግ እና በኔዘርላንድስ የሚገኙ በርካታ ወንዞች እንዲጥለቀለቁ አድርጓል፤ በዚህም የተነሳ ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ጎርፉ ያስከተለው ጉዳት ገና በመጣራት ላይ ነው። ይህ ጎርፍ እነዚህ አገሮች ባለፉት መቶ ዓመታት ካጋጠሟቸው እጅግ ከባድ የሚባሉ የጎርፍ አደጋዎች አንዱ ነው።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • ከወንድሞቻችን መካከል ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰበት ወይም ሕይወቱን ያጣ የለም

  • ቢያንስ 304 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

  • 100 ገደማ የሚሆኑ ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • ቢያንስ 242 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 11 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 4 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፤ ኮሚቴዎቹ የተቋቋሙት አንዱ ለቤልጅየም፣ ሁለቱ ለጀርመን እና ለሉክሰምበርግ፣ አንዱ ደግሞ ለኔዘርላንድስ ነው

  • በአሁኑ ወቅት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ የጽዳት እና የእድሳት ሥራውን እያስተባበሩ ነው፤ ሥራው ቤቶችን ማድረቅንና ጭቃውን ማስወገድን እንዲሁም አስቸኳይ የሆኑ የጥገና ሥራዎች ማከናወንን ይጨምራል

  • የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ እና የጉባኤ ሽማግሌዎች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ አስፋፊዎች ጊዜያዊ መጠለያና የመጠጥ ውኃ እንዲያገኙ አድርገዋል

  • በአካባቢው ያሉት የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በአደጋው ለተጎዱት ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ እና ስሜታዊ ድጋፍ እየሰጡ ነው

  • በኢንተርኔት አማካኝነት የሚካሄዱት የጉባኤ ስብሰባዎች አልተቋረጡም። የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በአደጋው ለተጎዱት አስፋፊዎች ማጽናኛ እና ማበረታቻ እየሰጡ ነው

  • ሁሉም የእርዳታ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የወጡትን የደህንነት ደንቦች ባገናዘበ መልኩ ነው

በኔዘርላንድስ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች አንዲትን አረጋዊት እህት ከቤታቸው ወጥተው ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ እንዲሄዱ ረዷቸው። ከዚያም ወንድሞች የእህትን ደህንነት ለማሳወቅ የእኚህን እህት ልጅ አነጋገሩት፤ ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር አይደለም። በኋላም ይህ ሰው ለእናቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ግሩም ሃይማኖት ውስጥ ነው ያለሽው። በጣም ይንከባከቡሻል!”

በቤልጅየም የእሳት አደጋ ሠራተኞች ወንድሞቻችን የሚያከናውኑትን የእርዳታ ሥራ ተመልክተው ነበር። እነዚህ ሠራተኞች፣ ወንድሞቻችን የደህንነት ትጥቆችን በማሟላታቸውና በሚገባ የተደራጁ በመሆናቸው አመሰገኗቸው። በጀርመን ያሉ የእሳት አደጋ ሠራተኞችም ወንድሞቻችን የእሳት አደጋ ሠራተኞች የሚሰጧቸውን መመሪያ ለመቀበል ባሳዩት ፈቃደኝነት ተደንቀዋል። አንዱ ሠራተኛ “እንደ እናንተ ያሉ ሰዎች ሁሉም ቦታ ቢኖሩ እንዴት ጥሩ ነበር” አላቸው።

በአደጋው የተጎዱት ወንድሞችና እህቶች ድርጅቱ ላደረገላቸው እርዳታ አመስጋኝ ናቸው። በተጨማሪም የይሖዋ ሕዝቦች ለአደጋ አስቀድመው እንዲዘጋጁ መመሪያ በመስጠቱ የበላይ አካሉን ያመሰግናሉ። በዋነኝነት የሚያመሰግኑት ግን ሕዝቦቹ ‘ተረጋግተው እንዲኖሩና መከራ ይደርስብናል የሚል ስጋት እንዳያድርባቸው’ የሚያደርገውን ይሖዋን ነው።—ምሳሌ 1:33