በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አንድ ወንድም የማላዊ ሐይቅ ላይ በታንኳ ሆኖ የጉባኤ ስብሰባ ቪዲዮዎችን ሲያወርድ

ታኅሣሥ 29, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የሚገኙ ወንድሞች የጉባኤ ስብሰባዎችን ለማድረግ የሚጠቀሙበት ብልሃትና የሚያደርጉት ጥረት

ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የሚገኙ ወንድሞች የጉባኤ ስብሰባዎችን ለማድረግ የሚጠቀሙበት ብልሃትና የሚያደርጉት ጥረት

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ጉባኤዎች በዚህ ወረርሽኝ ወቅት የጉባኤ ስብሰባዎችን ለማድረግ በኢንተርኔት ይጠቀማሉ። ይሁንና የኢንተርኔት አገልግሎት በሌለባቸው ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ አንዳንድ ወንድሞቻችን፣ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ የደህንነት ደንቦችን ሳይጥሱ የጉባኤ ስብሰባዎችን አዘውትረው ለማካሄድ ልዩ ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸዋል። እስቲ ከአፍሪካ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ማላዊ

ብዙ ወንድሞችና እህቶች የኢንተርኔት አገልግሎት ስለማያገኙ ዙም መጠቀም አይችሉም። የማላዊ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ በቪዲዮ የተቀረጸውን ስብሰባ በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ ላሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች በሞባይል ስልክ ኢንተርኔት አማካኝነት በየሳምንቱ ይልካል። ሽማግሌዎቹ ደግሞ ቪዲዮዎቹን ለጉባኤያቸው አስፋፊዎች ያሰራጫሉ።

ይሁንና በሰሜናዊ ማላዊ በሚገኘው ቻሮ ጉባኤ ያሉት 28 አስፋፊዎች ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ ለመሆን ይቸገራሉ፤ እነዚህ አስፋፊዎች የሚኖሩት በማላዊ ሐይቅ አቅራቢያ ባለው ተራራማ አካባቢ ነው። ተራሮቹ በአካባቢው የሞባይል ኔትዎርክ እንዳይደርስ ስለሚያግዱ ከሽማግሌዎቹ አንዱ ጥሩ ኔትዎርክ ለማግኘት በርካታ ኪሎ ሜትሮች ይጓዛል። ከዚያም ወደ ተራራማው አካባቢ ይመለስና ወደ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ቤት ቀረብ ብሎ ቪዲዮውን በገመድ አልባ ብሉቱዝ አማካኝነት ይልካል።

በቅርቡ ግን ሽማግሌዎቹ ከቤታቸው ብዙም ሳይርቁ ጥሩ ኔትወርክ ማግኘት የሚችሉበት ቦታ አግኝተዋል፤ ይህ ቦታ ማላዊ ሐይቅ ነው! ወንድሞች በታንኳ ተሳፍረው ወደ ሐይቁ መሃል በመሄድ ከተራሮቹ ሲርቁ ቪዲዮዎችን ለማውረድ የሚያስችል ኔትወርክ ያገኛሉ። ይህም ረጅም ሰዓት ከመጓዝ ያድናቸዋል።

ሞዛምቢክ

የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በሰሜን ምዕራብ ሞዛምቢክ ውስጥ ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎችን “ሲጎበኙ” ንግግራቸውን የሚያቀርቡት በሞባይል ስልክ አማካኝነት ነው። አብዛኛውን ጊዜ የኮንፈረንስ ጥሪ ማድረግ ስለማይቻል የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ከፊታቸው ብዙ ስልክ ደርድረው ንግግር ሲሰጡ ማየት የተለመደ ነው፤ በእያንዳንዱ ስልክ ከአንድ ቤተሰብ ጋር ይደዋወላሉ።

የወረዳ የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም አሊክ ካዛዌ ንግግር ሲያቀርብ። በእያንዳንዱ ስልክ አማካኝነት በሚጎበኘው ጉባኤ ካለ አንድ ቤተሰብ ጋር ተደዋውሏል

አንዳንድ አስፋፊዎች ግን የሚኖሩት በጣም ሩቅ በሆነ አካባቢ ስለሆነ ቤታቸው አቅራቢያ የስልክ ኔትወርክ የለም። ስለዚህ የስብሰባ ሰዓት ሲደርስ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ኔትወርክ እስኪያገኙ ድረስ ጫካ ውስጥ ይጓዛሉ። ከዚያም ኔትወርክ ባገኙበት ቦታ ላይ ቁጭ ብለው ስብሰባውን ያዳምጣሉ።

በዚያ አካባቢ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ዮሃኔ ቪኒዮ “በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከስብሰባዎች ጥቅም ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት” ስለሚያደርጉ ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር ቢራራቁም በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው መቀጠል እንደቻሉ ገልጿል። ካርሎስ ኮርታዛው የተባለ ሌላ የወረዳ የበላይ ተመልካች ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አሁንም ቢሆን ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በስብሰባ አዳራሽ እንደምንሰበሰብ፣ ሐሳብ እንደምንሰጥ እና አብረን እንደምንዘምር ሆኖ ይሰማናል። በዚህ ወረርሽኝ ወቅት በመንፈሳዊ መመገባችንን መቀጠል መቻላችን የይሖዋን እጅ እንድናይ አድርጎናል።”—ዮሐንስ 21:17