ሐምሌ 3, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
ሰኔ 28, 2020 ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወጡ
ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ በተፋፋመበት በዚህ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማውጣታቸውን ቀጥለዋል። ሰኔ 28, 2020 አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በአራት ቋንቋዎች ማለትም በስዋቲ፣ በጾንጋ፣ በዙሉና በቺቶንጋ ወጣ። በተጨማሪም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቤሊዝ ክሪዮልና በቶተናክ ቋንቋዎች ወጥቷል። ወንድሞቻችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አንድ ላይ መሰብሰብ ባይችሉም መጽሐፍ ቅዱሶቹን በኤሌክትሮኒክ ፎርማት ማግኘት በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቹ መውጣታቸው የተገለጸው ቀደም ብለው በተቀረጹ ንግግሮች አማካኝነት ሲሆን አስፋፊዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወይም በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት አማካኝነት ንግግሮቹን ተከታትለዋል።
ስዋቲ፣ ጾንጋ እና ዙሉ
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በስዋቲ ቋንቋ፣ የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በጾንጋ እና በዙሉ ቋንቋዎች በኤሌክትሮኒክ ፎርማት መውጣቱን አብስሯል። (ከላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) በደቡብ አፍሪካና በኤስዋቲኒ የሚኖሩ አስፋፊዎች ይህን ልዩ ፕሮግራም ተከታትለዋል።
በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ ከ38,000 በላይ የሚሆኑ አስፋፊዎችን ጨምሮ 18.5 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የስዋቲ፣ የጾንጋ እና የዙሉ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሚኖሩ ይገመታል።
ቺቶንጋ (ማላዊ)
የማላዊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኦገስቲን ሴሞ ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቺቶንጋ (ማላዊ) ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል።
የትርጉም ቡድኑ መጽሐፍ ቅዱሱን ተርጉሞ ለማጠናቀቅ ከሁለት ዓመት በላይ በትጋት ሠርቷል። አንዲት ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “የቺቶንጋ ቋንቋ ሦስት ቀበልኛዎች አሉት። በአንዱ አካባቢ የሚኖሩት ሰዎች የሚጠቀሙባቸው ቃላት በሌላ አካባቢ ለሚኖሩት ሰዎች እንግዳ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ አብዛኞቹ ሰዎች ሊረዱ የሚችሏቸውን ቃላት በጥንቃቄ ለመምረጥ ጥረት አድርገናል። በተጨማሪም ለአንባቢዎች እንግዳ ሊሆኑ የሚችሉ አገላለጾችን ለማብራራት የግርጌ ማስታወሻዎችን ተጠቅመናል።”
ሌላ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “አስፋፊዎች ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ለአገልግሎት ወይም ለስብሰባ መጠቀም ቀላል ይሆንላቸዋል፤ ቋንቋው ግልጽ ስለሆነ ለማንበብና ለመረዳት አይከብድም።”
ቤሊዝ ክሪዮል
የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆሹዋ ኪልጎር የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቤሊዝ ክሪዮል ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። ከ1,300 የሚበልጡ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
ስድስት ተርጓሚዎች ለአንድ ዓመት ከአራት ወር ያህል በዚህ ፕሮጀክት ላይ ተካፍለዋል። ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያለውን ጥቅም አስመልክቶ አንዷ ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ትክክለኛና እምነት የሚጣልበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘት ችለዋል። ይህ ትርጉም ግንዛቤያቸውን የሚጨምር መብራት ይሆንላቸዋል።”
አንዲት ሌላ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መሃል ቤሊዝ ክሪዮልን የሚናገሩ ወንድሞችና እህቶች ቅዱሳን መጻሕፍትን በቋንቋቸው ማንበብ ይችላሉ። ይህም የተጨነቀውን ልባቸውን ለማረጋጋትና ወደፊት የሚያጋጥማቸውን ችግር በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም ይረዳቸዋል።”
ቤሊዝ ውስጥ በቤሊዝ ክሪዮል ቋንቋ በሚመሩ 19 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 867 አስፋፊዎች አሉ። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደግሞ በቤሊዝ ክሪዮል ቋንቋ መስክ የሚያገለግሉ 58 አስፋፊዎች አሉ።
ቶተናክ
የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጄሲ ፔሬዝ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቶተናክ ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ በሚገኙት በቶተናክ ቋንቋ የሚመሩ 50 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 2,200 ገደማ አስፋፊዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
የትርጉም ቡድኑ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት ገደማ ወስዶበታል። ይህ ትርጉም ሜክሲኮ ውስጥ ለሚገኙት ከ250,000 የሚበልጡ የቶተናክ ቋንቋ ተናጋሪዎች ምሥራቹን ለመስበክ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ይጠበቃል።
አንድ ተርጓሚ እንደተናገረው በቶተናክ ቋንቋ ከተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተለየ መልኩ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም “የሚጠቀመው በዕለት ተዕለት የምንጠቀምበትን ቋንቋ ነው።” አክሎም “አሁን በክልላችን ውስጥ ለሚኖሩት ሰዎች የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮችን ማስረዳት ቀላል ይሆንልናል” ብሏል።
“ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲህ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማግኘት በጉጉት ሲጠብቁ ነበር” በማለት ሌላ ተርጓሚ ተናግሯል። “እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንዳንድ አስፋፊዎች በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ክፍል ሲያቀርቡ አንዳንድ ጥቅሶችን ከስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ቶተናክ ይተረጉሙ ነበር። ከአሁን በኋላ ግን ከግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲጠቅሱ እንዲህ ማድረግ አያስፈልጋቸውም።”
ይህ ትርጉም ያለው አንድ ጠቃሚ ገጽታ የአንዳንድ ቃላትን ተለዋጭ ትርጉሞች በግርጌ ማስታወሻዎቹ ላይ ማስቀመጡ ነው። በግርጌ ማስታወሻዎቹ ላይ የሚቀመጡት አገላለጾች የቶተናክ ቋንቋ ቀበልኛዎችን የሚናገሩ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው አገላለጾች ስለሆኑ ይህ ትርጉም ቋንቋውን ለሚናገሩ ሰዎች በሙሉ በቀላሉ ይገባል።
በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ካገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አብረን ተደስተናል። ወንድሞቻችን ይህን ‘የመንፈስ ሰይፍ’ በአገልግሎታቸውና በግል ጥናታቸው ላይ ሲጠቀሙበት እምነታቸው እንደሚጠናከር እርግጠኞች ነን።—ዕብራውያን 4:12