በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 1, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በመስከረም 2024 በዓለም ዙሪያ ሰባት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወጡ

በመስከረም 2024 በዓለም ዙሪያ ሰባት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወጡ

በጣሊያን ምልክት ቋንቋ

የጣሊያን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ማሲሚሊያኖ ብሪኮኒ መስከረም 1, 2024 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በጣሊያን ምልክት ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። ዜናው የተበሰረው ሮም፣ ጣሊያን ውስጥ በትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በተደረገው “ምሥራቹን አውጁ!” በተባለው የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ሲሆን 854 ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር። መጽሐፍ ቅዱሱ ወዲያውኑ በ​jw.org እና በ​Jw Library Sign Language አፕሊኬሽን ላይ እንዲወጣ ተደርጓል።

ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በጣሊያን ምልክት ቋንቋ ሲተረጎም ይህ የመጀመሪያው ነው። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን በጣሊያን ምልክት ቋንቋ ማዘጋጀት የጀመሩት በ1998 ነበር። በአሁኑ ወቅት በመላዋ ጣሊያን በጣሊያን ምልክት ቋንቋ በሚካሄዱ 15 ጉባኤዎች፣ 12 ቡድኖችና 10 ቅድመ ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 845 ወንድሞችና እህቶች አሉ።

ሩቶሮ

የኡጋንዳ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፍሬደሪክ ንዬንዴ መስከረም 6, 2024 የማቴዎስ፣ የማርቆስ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች በሩቶሮ ቋንቋ መውጣታቸውን አብስሯል። ይህ ዜና የተበሰረው “ምሥራቹን አውጁ!” በተባለውና በሆይማ፣ ኡጋንዳ በተደረገው የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል የታተመ ቅጂ በስብሰባው ላይ ለተገኙት 928 ታዳሚዎች ታድሏል። በተጨማሪም አራቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ወዲያውኑ በ​jw.org እና በ​jw Library አፕሊኬሽን ላይ ተለቅቀዋል።

ኡጋንዳ ውስጥ 2.2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ሩቶሮ ወይም ተቀራራቢ ቋንቋ የሆነውን ሩንዮሮ እንደሚናገሩ ይገመታል። በእነዚህ ቋንቋዎች በተዘጋጁት አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም አይገኝም። ኡጋንዳ ውስጥ በሩቶሮ ቋንቋ በሚካሄዱ ሁለት ጉባኤዎችና በሩንዮሮ ቋንቋ በሚካሄዱ አራት ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 374 ወንድሞችና እህቶች ይገኛሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በአገልግሎትና በስብሰባዎች ላይ ሊጠቀሙበት የሚችሉ፣ ትክክለኛና ግልጽ የሆነ እንዲሁም አራቱን ወንጌሎች ያጠቃለለ ትርጉም በማግኘታቸው የተሰማቸው ደስታ ወደር የለውም።

ዊገር (አረብኛ) እና ዊገር (ሲሪሊክ)

መስከረም 8, 2024 በአልማቲ፣ ካዛክስታን በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በተደረገ ልዩ ዝግጅት ላይ የማቴዎስ ወንጌል በዊገር (አረብኛ) እና በዊገር (ሲሪሊክ) መውጣቱ ተበስሯል። በዝግጅቱ ላይ 483 ሰዎች ተገኝተዋል። የማቴዎስ ወንጌል ወዲያውኑ በ​jw.org እና JW Library አፕሊኬሽን ላይ በሁለቱም ቋንቋዎች ወጥቷል።

በዊገር (አረብኛ) እና በዊገር (ሲሪሊክ) ቋንቋዎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይገኛሉ፤ ሆኖም የሚጠቀሙበት ቋንቋ ጊዜ ያለፈበትና ለመረዳት የሚከብድ ነው። ዊገር ተናጋሪ ከሆኑት 11 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአሁኑ ወቅት የሚኖሩት በእስያ ነው። ሆኖም በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካም ጭምር ዊገር ቋንቋ ተናጋሪዎች አሉ።

ሉኮንዞ

የኡጋንዳ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሞሰስ ኦዉንዶ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሆኑት የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች በሉኮንዞ ቋንቋ መውጣታቸውን መስከረም 13, 2024 አብስሯል። ዜናው የተበሰረው “ምሥራቹን አውጁ!” በተባለውና ብዌራ፣ ኡጋንዳ ውስጥ በተካሄደው የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ነው፤ በስብሰባው ላይ 925 ሰዎች ተገኝተዋል። ሁሉም ታዳሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል የታተመ ቅጂ እንዲደርሳቸው ተደርጓል። እንዲሁም በዚያው ጊዜ አራቱንም የወንጌል ዘገባዎች ከ​jw.org እና ከ​JW Library አፕሊኬሽን ላይ ማውረድ ተችሏል።

ከአንድ ሚሊዮን የማያንሱ የኡጋንዳ ነዋሪዎች ሉኮንዞ ቋንቋ ይናገራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን በሉኮንዞ ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ2001 ነበር። በአሁኑ ወቅት በስድስት የሉኮንዞ ቋንቋ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 324 ወንድሞችና እህቶች አሉ።

የላይቤሪያ እንግሊዝኛ

የላይቤሪያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጄትሮ በርክሌይ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሆኑት የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌሎች በላይቤሪያ እንግሊዝኛ መውጣታቸውን መስከረም 15, 2024 አብስሯል። ዜናው የተነገረው በጆንሰንቪል፣ ላይቤሪያ በሚገኝ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በተከናወነ ልዩ ዝግጅት ላይ ነበር። በልዩ ዝግጅቱ ላይ የተገኙት ታዳሚዎች ብዛት 1,176 ነበር። እንዲሁም በመላዋ ላይቤሪያ የሚገኙ በላይቤሪያ እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚካሄዱ ጉባኤዎች ሁሉ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን እንዲከታተሉ ፈቃድ ተሰጥቶ ነበር። በዚያው ወቅት የሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ኤሌክትሮኒክና የድምፅ ቅጂዎች በ​jw.org እና በ​Jw Library አፕሊኬሽን ላይ ተለቅቀዋል። በቅርቡ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በታተመ ቅጂ ይወጣል።

በላይቤሪያ እንግሊዝኛ በድምፅ የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ይገኛሉ። ሆኖም የአምላክ ቃል በጽሑፍ መልክ በላይቤሪያ እንግሊዝኛ ሲተረጎም ይህ የመጀመሪያው ነው። የላይቤሪያ የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም 1.6 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የላይቤሪያ እንግሊዝኛ እንደሚናገሩ ይገመታል፤ ይህ ቁጥር በ120 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት 7,034 ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንንም ይጨምራል።

ናዋትል (ጉዌሬሮ)

የማዕከላዊ አፍሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ላዛሮ ጎንዛሌዝ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሆኑት የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች በናዋትል (ጉዌሬሮ) ቋንቋ መተርጎማቸውን መስከረም 20, 2024 አብስሯል። ዜናው የተነገረው “ምሥራቹን ስበኩ!” በተባለው በጉዌሬሮ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው ቺልፓንሲንጎ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ 769 ሰዎች የተገኙ ሲሆን በትላፓ ዴ ኮመንፎርት፣ ሜክሲኮ እየተካሄደ በነበረው የክልል ስብሰባ ላይ የተገኙ ሌሎች 742 ሰዎችም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን ተመልክተዋል። በሁለቱም ቦታዎች የተገኙት ሁሉም ተሰብሳቢዎች የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል ቅጂ ማግኘት ችለዋል፤ ሁሉም የወንጌል ዘገባዎች በ​jw.org እና JW Library አፕሊኬሽን ላይ ወዲያውኑ ተለቅቀዋል።

ሜክሲኮ ውስጥ 250,000 ገደማ ሰዎች ናዋትል (ጉዌሬሮ) ቋንቋ ይናገራሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በናዋትል (ጉዌሬሮ) የሚካሄድ ጉባኤ የተቋቋመው በ1987 ነበር። በአሁኑ ወቅት በናዋትል (ጉዌሬሮ) ቋንቋ በሚካሄዱ 37 ጉባኤዎችና 2 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 1,216 ወንድሞችና እህቶች ይገኛሉ።