ጥቅምት 28, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና
በሩሲያና በክራይሚያ እስር ቤት የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ100 አለፈ
እስከ ጥቅምት 26, 2022 ድረስ ያለው ሪፖርት እንደሚጠቁመው በሩሲያና በክራይሚያ 106 ወንድሞችና 4 እህቶች በእምነታቸው ምክንያት ወህኒ ወይም ማረፊያ ቤት ታስረው ይገኛሉ። የ44 ዓመቱ ዲሚትሪ ዶልዢኮቭ ከታሰሩት የይሖዋ አገልጋዮች 100ኛው ሆኗል። ዲሚትሪ የታሰረው መስከረም 8, 2022 ነው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘቱና እምነቱን ለሌሎች በመናገሩ በጽንፈኛ ድርጅት እንቅስቃሴ ተሳትፈሃል ተብሎ ተከሰሰ። በ2017 ከተጣለው እገዳ ወዲህ በድምሩ ወደ 350 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች እስር ቤት ገብተዋል።
ፖሊሶች በቼልያቢንስክ ክልል የሚገኘውን የዲሚትሪ መኖሪያ ቤት ከበረበሩ በኋላ ይዘውት ሄዱ። ከሁለት ቀን በኋላ በኖቮሲቢርስክ ክልል ወደሚገኝ ማረፊያ ቤት ተወሰደ፤ ይህ ቦታ ከመኖሪያ ቤቱ 1,500 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል።
ዲሚትሪ ከ12 ሰዎች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ታስሯል። ባለቤቱ ማሪና ሄዳ እንድትጠይቀው አልተፈቀደላትም፤ ሆኖም ደብዳቤ መጻጻፍ ይችላሉ።
ማሪና እንዲህ ብላለች፦ “ይዘውት የሄዱ ሰሞን እንቅልፍ አልነበረኝም፤ ብዙውን ጊዜ ሌሊት ያባንነኝ ነበር። በጉባኤያችን ያሉ ወዳጆቼ ለተወሰነ ጊዜ እነሱ ጋ እንድቆይ ጋበዙኝ፤ ይህም በጣም ጠቅሞኛል።”
ዲሚትሪ በጥሩ ስሜት ላይ እንደሚገኝ ማሪና ተናግራለች። “ይሖዋ እየተንከባከበው ነው” ብላለች።
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ክስ የተመሠረተባቸው በሩሲያ ፌዴሬሽን የወንጀለኛ መቅጫ ላይ ስለ ጽንፈኝነት የሚገልጸውን ሕግ መሠረት በማድረግ ነው። ከታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል የ57 ዓመቷ አና ሳፍሮኖቫ ትገኝበታለች፤ የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶባታል። እንዲህ ያለ ረጅም የእስራት ጊዜ በእህቶች ላይ ሲበየን ይህ የመጀመሪያው ነው።
የዲሚትሪ እስራት ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የከፈተችው አሳፋሪ የስደት ዘመቻ ሌላ ምዕራፍ ላይ የደረሰበት ነው፤ ሩሲያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ውግዘት ችላ በማለት ላለፉት አምስት ዓመታት በዚህ ድርጊቷ ገፍታበታለች። የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2017 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያስተላለፈው ብይን የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ተቋማት እንዲዘጉ የሚጠይቅ እንጂ የግለሰቦችን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚነካ እንዳልሆነ የሩሲያ ባለሥልጣናት ገልጸው ነበር። ሆኖም እውነታው ከዚህ ይለያል። እስካሁን ድረስ ወደ 700 በሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ 308 የክስ መዝገቦች ተከፍተዋል። በተጨማሪም በ1,851 የይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያ ቤቶች ላይ ብርበራ ተካሂዷል።
ለዲሚትሪም ሆነ በእምነታቸው ምክንያት ስደት ለሚደርስባቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሁሉ እየጸለይን ነው። ይሖዋ ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ኃይል እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ነን።—ማቴዎስ 24:13