በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 17, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በሰኔ 2024 በዓለም ዙሪያ ስድስት መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ

በሰኔ 2024 በዓለም ዙሪያ ስድስት መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ

ጓዴሎፕኛ ክሪኦል

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ዊንደር ሰኔ 9, 2024 የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌሎች በጓዴሎፕኛ ክሪኦል መውጣታቸውን አብስሯል፤ የመጻሕፍቱ መውጣት የተገለጸው በቤይ ማዉ፣ ጓዴሎፕ በተደረገው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የ2024 ልዩ የክልል ስብሰባ የመደምደሚያ ንግግር ላይ ነው። በስብሰባው ላይ በአጠቃላይ 8,602 ሰዎች ተገኝተዋል። ሌሎች 5,588 ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። በአካል የተገኙት ተሰብሳቢዎች የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል ቅጂ አግኝተዋል። ሁለቱንም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያው ማውረድ ተችሏል።

በጓዴሎፕ ከ300,000 በላይ፣ በፈረንሳይ ደግሞ 200,000 የጓዴሎፕኛ ክሪኦል ተናጋሪዎች አሉ። በአሁኑ ወቅት 3,300 ገደማ የሚሆኑ የጓዴሎፕኛ ክሪኦል ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች በጓዴሎፕ በሚገኙት 42 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ፤ በፈረንሳይ በሚገኙት 2 ቡድኖች ውስጥ ደግሞ 80 ወንድሞችና እህቶች ያገለግላሉ።

አርመንኛ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ሰኔ 28, 2024 የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በአርመንኛ መውጣቱን አብስሯል። a ይህ ማስታወቂያ የተነገረው በየረቫን፣ አርሜንያ አቅራቢያ በተደረገው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የ2024 የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ ነው። በአጠቃላይ 6,155 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። በአርመንኛ የወጣውን የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የኤሌክትሮኒክ ቅጂ ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያውኑ ማውረድ ተችሏል። የታተመው ቅጂም በዚሁ ዓመት ይደርሳል።

የመጀመሪያው አርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመው በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ነበር። ሙሉው የአርመንኛ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ መጀመሪያ የወጣው በ2010 ነበር። በአሁኑ ወቅት ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ አርመንኛ ተናጋሪዎች አርሜንያ ውስጥ ይኖራሉ፤ ከእነዚህም መካከል በ117 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 10,550 ገደማ ወንድሞችና እህቶች ይገኙበታል። ሌሎች 5,200 ወንድሞችና እህቶች ደግሞ በመላው አውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ አርመንኛ ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ ያገለግላሉ።

ፋንቴ

የጋና ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፍሪማን አቢ ሰኔ 28, 2024 የማቴዎስ ወንጌል በፋንቴ ቋንቋ መውጣቱን አስታወቀ፤ ማስታወቂያው የተነገረው በሴኮንዲ ታኮራዲ፣ ጋና በሚገኘው በታኮራዲ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በተካሄደው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ነው። በፕሮግራሙ ላይ 1,230 ወንድሞችና እህቶች በአካል ተገኝተዋል። ሌሎች 2,022 ተሰብሳቢዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታትለዋል። በአካል የተገኙት ተሰብሳቢዎች የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል ቅጂ አግኝተዋል። የኤሌክትሮኒክ ቅጂውን ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይም ወዲያው ማውረድ ተችሏል።

ስድስት ሚሊዮን ገደማ የፋንቴ ተናጋሪዎች እንዳሉ ይገመታል። አሁን ሴኮንዲ ታኮራዲ፣ ጋና በሚባለው ቦታ የመጀመሪያው የፋንቴ ቋንቋ ጉባኤ የተቋቋመው መስከረም 1935 ነበር። ዛሬ 9,700 ፋንቴ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች በጋና በሚገኙ 158 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ።

አይስላንድኛ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን ሰኔ 28, 2024 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በአይስላንድኛ መውጣቱን አብስሯል፤ ይህ ማስታወቂያ የተነገረው በሬይኪቪክ፣ አይስላንድ በተደረገው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የ2024 ልዩ የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ ነው። በስብሰባው ላይ የተገኙት 1,312 ተሰብሳቢዎች የአዲሱ ዓለም ትርጉም የታተመ ቅጂ ተሰጥቷቸዋል። ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይም የኤሌክትሮኒክ ቅጂውን ወዲያው ማውረድ ተችሏል።

በ2019 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአይስላንድኛ ወጥቶ ነበር። በአምስት ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት 395 አይስላንድኛ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች ሙሉውን አዲስ ዓለም ትርጉም በማግኘታቸው ተደስተዋል፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ 390,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች ባሏት በዚህች ደሴት ለሚያከናውኑት አገልግሎትም ይጠቅማቸዋል።

ንጋንጌላ

የአንጎላ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዮሐንስ ደ ያገር ሰኔ 28, 2024 የማቴዎስ፣ የሉቃስና የሐዋርያት ሥራ መጻሕፍት በንጋንጌላ ቋንቋ መውጣታቸውን አበሰረ። ይህ ማስታወቂያ የተነገረው በሜኖንጊ፣ አንጎላ በተደረገው ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የ2024 የክልል ስብሰባ ላይ ነው። በስብሰባው ላይ የተገኙት 450 ተሰብሳቢዎች የማቴዎስ ወንጌል የታተመ ቅጂ ተሰጥቷቸዋል። የሦስቱንም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ኤሌክትሮኒክ ቅጂ ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያው ማውረድ ተችሏል።

አንጎላ ውስጥ አንድ ሚሊዮን የንጋንጌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። በንጋንጌላ ቋንቋ የሚመራው የመጀመሪያው ጉባኤ የተቋቋመው በ2011 ነው። በአሁኑ ወቅት 260 ወንድሞችና እህቶች በአንጎላ እና በናሚቢያ ባሉት በንጋንጌላ ቋንቋ የሚመሩ ስምንት ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ ያገለግላሉ።

ንጋቤሬ

የማዕከላዊ አሜሪካ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ካርሎስ ማርቲኔዝ ሰኔ 30, 2024 መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በንጋቤሬ ቋንቋ መውጣቱን አስታውቋል፤ መጽሐፉ መውጣቱ የተገለጸው አስቀድሞ በተቀዳ ፕሮግራም አማካኝነት ሲሆን ፕሮግራሙ በኮስታ ሪካ እና በፓናማ ወደሚገኙ የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾች ተላልፏል። በእነዚህ ቦታዎች ሆነው ፕሮግራሙን የተከታተሉት 2,032 ተሰብሳቢዎች ማስታወቂያው ከተነገረ በኋላ የማቴዎስ ወንጌል የታተመ ቅጂ ተሰጥቷቸዋል። የኤሌክትሮኒክ ቅጂውን ከ​jw.org እና ከ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ወዲያውኑ ማውረድ ተችሏል።

በአሁኑ ጊዜ በዋነኝነት በኮስታ ሪካ እና በፓናማ የሚኖሩ 216,000 ገደማ የንጋቤሬ ቋንቋ ተናጋሪዎች አሉ። በእነዚህ አገራት የሚኖሩት 877 የንጋቤሬ ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በ26 ጉባኤዎችና በ2 ቡድኖች ውስጥ ያገለግላሉ።

a የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በምሥራቅ አርመንኛ ቀደም ሲል ወጥቷል፤ ይህ ቋንቋ ከአርሜንያ ውጭ በሚኖሩ በርካታ አርመንኛ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ውስጥ ከሚነገረው የምዕራብ አርመንኛ ይለያል።