መጋቢት 21, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና
በቦሊቪያ እና በኮሎምቢያ ልዩ የስብከት ዘመቻ ተካሄደ
ከኅዳር 1, 2023 እስከ ጥር 31, 2024 በመላው ቦሊቪያ እና ኮሎምቢያ ከ19,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የተሳተፉበት ልዩ የስብከት ዘመቻ ተካሂዷል። በዘመቻው ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው የተስፋ መልእክት በስፓንኛ እንዲሁም የቦሊቪያ እና የኮሎምቢያ የምልክት ቋንቋዎችን ጨምሮ በ18 ሌሎች ቋንቋዎች ተሰብኳል።
ወንድሞች ጓዳሉፔ፣ ኮሎምቢያ ውስጥ በስፓንኛ ሲያገለግሉ አንድ ቤት አንኳኩ፤ አንዲት ሴት በሩን ከፍታ “ስንጠብቃችሁ ነበር እኮ!” አለቻቸው። ከጥቂት ቀናት በፊት አንዳንድ ሃይማኖታዊ በዓላትን ማክበር ትክክል እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ከባለቤቷ ጋር ሲነጋገሩ እንደነበር ነገረቻቸው። የሴትየዋ ባል፣ ወንድሞቻችንን በአቅራቢያው ሲሰብኩ እንዳያቸው፣ የእነሱም ቤት መምጣታቸው እንደማይቀርና ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንደሚሰጧቸው ነግሯት ነበር። ወንድሞቻችን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ የሚያስተምረውን ነገር በደስታ አስረዷቸው፤ ሌላ ሰው መጥቶ በቀጣይነት እንዲረዳቸውም ዝግጅት አደረጉ።
ቦሊቪያ ውስጥ ኳትሮ ካኛዳስ በተባለች ትንሽ ከተማ ሁለት እህቶች ሲሰብኩ ሱቅ ደጃፍ ላይ ሚጌሊና የተባለች ሴት አነጋገሩ። ይህች ሴት በቅርቡ ሐዘን እንደደረሰባት ሲያውቁ ራእይ 21:3, 4ን አነበቡላት። ሚጌሊና መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች። ችግሩ ግን፣ የምትኖረው ራቅ ባለ ገለልተኛ አካባቢ ሲሆን ስልክ የላትም። እነዚሁ ሁለት እህቶች ከተወሰኑ ቀናት በኋላ በዚችው ትንሽ ከተማ ዳርቻ ላይ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ አንዲት ወጣት ሴት አነጋገሩ። የሚገርመው፣ ሚጌሊና ከዚያው ቤት ስትወጣ አገኟት። እህቶች፣ የሚያነጋግሯት ወጣት የሚጌሊና ልጅ እንደሆነች ሲያውቁ ተገረሙ። ሁሉም በጣም ተደሰቱ! መላ ቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲጀምር ዝግጅት ተደረገ።
ይሖዋ በዘመቻው የተካፈሉ ወንድሞችና እህቶች ያደረጉትን ጥረት ሲመለከት ምንኛ ተደስቶ ይሆን! አገልጋዮቹ ምሥራቹን “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” ለመስበክ የሚያደርጉትን ጥረት መባረኩን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—ቆላስይስ 1:23