በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 8, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በትርጉም ሥራ አዲስ ሪከርድ ተመዘገበ—በሁለት ቀናት 13 መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ

በትርጉም ሥራ አዲስ ሪከርድ ተመዘገበ—በሁለት ቀናት 13 መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ

ሰኔ 25-26, 2022 በትርጉም ሥራ አዲስ ታሪክ አስመዝግበናል፤ አዲስ ዓለም ትርጉም በ13 ቋንቋዎች ወጥቷል። ከአሁን በፊት በአንድ ቅዳሜና እሁድ መጽሐፍ ቅዱሶች ያወጣነው በስድስት ቋንቋዎች ነበር። አዲስ ስለተመዘገበው ታሪካዊ ክንውን የሚገልጽ ሪፖርት ከዚህ በታች ቀርቧል።

ጼልታል

የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አርማንዶ ኦቾዋ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በጼልታል ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። ፕሮግራሙ 1,400 ገደማ ለሚሆኑ ሰዎች ተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱሱ የወጣው በታተመና በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ነው።

ከጼልታል ተርጓሚዎች አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “መለስ ብዬ ሳስበው በዚህ ሥራ ላይ የይሖዋን እጅ በደንብ አይቻለሁ። የተከናወነው ነገር በጣም ያስደንቀኛል። ሥራውን ማጠናቀቅ የቻልነው የይሖዋ መንፈስ ስለረዳን ብቻ ነው።”

ዋዩናይኪ

የኮሎምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ የሆነው ወንድም ካርሎስ ሞሬኖ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (ከማቴዎስ እስከ ሐዋርያት ሥራ) በዋዩናይኪ ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። አስቀድሞ የተቀረጸው ፕሮግራም በኮሎምቢያ እና በቬኔዙዌላ ለሚገኙ 2,000 ገደማ ሰዎች ተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱሱ የወጣው በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ነው። የታተመው ቅጂ ወደፊት እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ባውሌ

የኮት ዲቩዋር ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ክሪስቶፕፍ ኩሉ ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በባውሌ ቋንቋ መውጣቱን አስታውቋል፤ አስቀድሞ የተቀዳው ፕሮግራም ከ12,000 ለሚበልጡ ሰዎች ተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱሱ የወጣው በኤሌክትሮኒክ መልክ ሲሆን የታተመው ቅጂ ጥቅምት 2022 ይደርሳል። በኮት ዲቩዋር ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር በሚነገሩ ቋንቋዎች ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው።

በትርጉም ሥራው ላይ የተካፈለ አንድ ወንድም ለሥራው ይበልጥ እንዲነሳሱ የረዳቸው ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሥራው ላይ አንድ አስቸጋሪ ነገር ሲያጋጥመን፣ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም በክልላችን ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ ሲያገኙ ምን ያህል እንደሚደሰቱ ለማሰብ እንሞክራለን። ይህን ማሰባችንና የይሖዋን እርዳታ ማግኘታችን በሥራው እንድንገፋ ብርታት ሰጥቶናል።”

ዌልሽ

የብሪታንያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፒተር ቤል የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዌልሽ ቋንቋ መውጣቱን አሳወቀ፤ ፕሮግራሙ በቀጥታ የተላለፈው በዌልስ ከሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ነው። በዌልስና በአርጀንቲና 2,057 የሚያህሉ ሰዎች በስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። ተሰብሳቢዎቹ በኤሌክትሮኒክ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ወዲያውኑ ማግኘት ችለዋል። የታተመው ቅጂ ታኅሣሥ 2022 ይደርሳል።

የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ስንተረጉም የተሰማንን ስሜት አልረሳውም። መለኮታዊውን ስም በትክክለኛው ቦታው መልሶ ማስገባት በጣም ትልቅ መብት ነው።”

ማንያዋ እና ቴዌ

የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ማርሴሎ ሳንቶስ መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በማንያዋ እና በቴዌ ቋንቋዎች መውጣቱን አስቀድሞ በተቀዱ ሁለት ፕሮግራሞች አሳውቋል። ፕሮግራሞቹ በ⁠JW ስትሪም ተላልፈዋል። በቴሌቪዥንና በሬዲዮም ተሰራጭተዋል። እነዚህ ትርጉሞች የወጡት በድምፅና በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ነው። የታተመው ቅጂ መስከረም 2022 ይደርሳል።

እስካሁን እንደሚታወቀው በማንያዋ ቋንቋ የተተረጎመው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ይህ ነው፤ በቴዌ ቋንቋም ቢሆን የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። እነዚህን ትርጉሞች የሚያነብቡና የሚያዳምጡ ሰዎች በእጅጉ ይጠቀማሉ።

ኬችዋ (አንካሽ)፣ ኬችዋ (አያኩቾ) እና ኬችዋ (ኩዝኮ)

የፔሩ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ማርሴሎ ሞያኖ አዲስ ዓለም ትርጉም በኬችዋ (አንካሽ)፣ በኬችዋ (አያኩቾ) እና በኬችዋ (ኩዝኮ) ቋንቋዎች በኤሌክትሮኒክ ቅጂ መውጣቱን አብስሯል። በፔሩ ከሚነገሩት የኬችዋ ቋንቋዎች ዋነኞቹ እነዚህ ሦስቱ ናቸው። አስቀድሞ የተቀረጸው ፕሮግራም ከ7,000 ለሚበልጡ ሰዎች ተላልፏል። የታተመው ቅጂ ጥቅምት 2022 ይደርሳል።

የኬችዋ ቋንቋዎች ምንጫቸው አንድ ቢሆንም በየአካባቢው የሚነገሩበት መንገድ ይለያያል፤ በመሆኑም አንባቢዎች መጽሐፍ ቅዱስን በግልጽ መረዳት እንዲችሉ የተለያዩ ትርጉሞችን ማዘጋጀት አስፈልጓል። ተርጓሚዎቹ በየአካባቢው የሚገኙት አንባቢዎች በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት ትርጉም ለማዘጋጀት ቃላቱን በጥንቃቄ መርጠዋል።

እንድቤሌ፣ ሴሶቶ (ሌሶቶ) እና ሴሶቶ (ደቡብ አፍሪካ)

የበላይ አካል አባል የሆነው ኬነዝ ኩክ አዲስ ዓለም ትርጉም በእንድቤሌ እና በሴሶቶ (ደቡብ አፍሪካ) ቋንቋዎች መውጣቱን አብስሯል። በተጨማሪም የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በሴሶቶ (ሌሶቶ) መውጣቱን አሳውቋል። አስቀድሞ የተቀረጸውን ይህን ፕሮግራም ከ28,000 በላይ ሰዎች ተከታትለውታል፤ ፕሮግራሙ በመላው አገሪቱ በሚገኙ የተመረጡ የስብሰባ አዳራሾችና መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ታይቷል። ተሰብሳቢዎቹ በኤሌክትሮኒክ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ወዲያውኑ ማግኘት ችለዋል፤ የታተመው ቅጂ ታኅሣሥ 2022 ይደርሳል። ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በእንድቤሌ እና በሴሶቶ (ደቡብ አፍሪካ) የወጣው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነ አንድ ወንድም በእንድቤሌ ስለተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በክልላችን ለሚገኙ እንድቤሌ ተናጋሪዎች ትልቅ በረከት ነው፤ ምክንያቱም የይሖዋን ስም በቦታው መልሶ አስገብቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ የአምላክን ስም ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ይችላሉ።”

እንድቤሌ (ዚምባብዌ)

የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሺንጊሬ ማፕፉሞ ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በእንድቤሌ (ዚምባብዌ) በኤሌክትሮኒክ ቅጂ መውጣቱን አሳውቋል። የታተመው ቅጂ ሐምሌ 2022 ይደርሳል። አስቀድሞ የተቀረጸው ይህ ፕሮግራም በመላው ዚምባብዌ ወደሚገኙ የስብሰባ አዳራሾች የተላለፈ ሲሆን ከ8,700 የሚበልጡ ሰዎች ተከታትለውታል።

በእንድቤሌ (ዚምባብዌ) የተዘጋጁ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቢኖሩም አዲስ ዓለም ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በግልጽ ለመረዳት ያስችላል። ለምሳሌ ዮሐንስ 17:3 ላይ ሌሎች የእንድቤሌ ትርጉሞች ኢየሱስ ክርስቶስን “እውነተኛው አምላክ” ብለውታል። አዲስ ዓለም ትርጉም ግን በይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ አስቀምጧል። አንድ ተርጓሚ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የተዘጋጀው ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚጠቀሙበት ቋንቋ ነው” ብሏል።

በመላው ዓለም እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች የአምላክን ቃል ማግኘታቸው ያስደስተናል፤ በገዛ ቋንቋቸው “የሕይወትን ውኃ በነፃ [መውሰድ]” ችለዋል።—ራእይ 22:17