ታኅሣሥ 31, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና
በኅዳር ወር በተደረገው ዘመቻ ለሕዝብ የሚሰራጨው ቁጥር 2 መጠበቂያ ግንብ ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተሰራጭቷል
መጽሔቱ በሰባት ተጨማሪ ቋንቋዎች ወጥቷል!
ኅዳር 2021 በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለሕዝብ የሚሰራጨውን ቁጥር 2 2021 መጠበቂያ ግንብ ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች አሰራጭተዋል። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ሰባቱ፣ ቁጥር 2 2021 መጠበቂያ ግንብ የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትማቸው ነው። እነዚህ ቋንቋዎች የሚከተሉት ናቸው፦ ሃዋይ ፒጅን፣ ሉክሰምበርግኛ፣ ማኒፑሪ (በላቲን ፊደላት)፣ ሴንት ሉችያን ክሪኦል፣ ኦዲያ፣ ፌሮኢስ እና ፖሜራንኛ።
በዋናው መሥሪያ ቤት የትርጉም አገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚሠራው ወንድም ኒኮላስ አላዲስ እንዲህ ብሏል፦ “በጽሑፎቻችን ውስጥ ያለው መረጃ በዓለም ዙሪያ ያሉ አንባቢዎችን ትኩረት የሚስብ ነው። አንዳንድ የትርጉም ቡድኖች ግን ሁኔታቸው ስለማይፈቅድላቸው ሁሉንም የመጠበቂያ ግንብ እትሞች መተርጎም ሊከብዳቸው ይችላል። እንዲህ ያሉ የትርጉም ቡድኖችን ሥራ የሚከታተሉ ቅርንጫፍ ኮሚቴዎች አንዳንድ ለየት ያሉ እትሞች እንዲተረጎሙ ለበላይ አካሉ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ። ቁጥር 2 2021 መጠበቂያ ግንብ በእነዚህ ቋንቋዎች የተተረጎመው በዚሁ ምክንያት ነው።”
እነዚህ ቋንቋዎች ከሚነገሩባቸው መስኮች የተገኙት ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ተሞክሮዎች በኅዳር ወር የተደረገው ዘመቻ እንዲሁም የተለያዩ ቋንቋዎችን ለሚናገሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን ለማድረስ የምናደርገው ጥረት ምን በጎ ውጤት እንዳስገኘ ያሳያሉ።
በዚህ ልዩ ዘመቻ አማካኝነት መጠበቂያ ግንብ መጽሔታችን ብዙ ሰዎች ጋ እንደደረሰ በማወቃችን በጣም ተደስተናል። እንዲህ ያሉ ዘመቻዎች “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” የሚፈልገውን የአምላካችንን ፈቃድ ለመደገፍ እንደሚያስችሉ እንገነዘባለን።—1 ጢሞቴዎስ 2:4