ኅዳር 14, 2019
ዓለም አቀፋዊ ዜና
በኦስትሪያ እና በጀርመን ለሚገኙ አረብኛ የሚናገሩ ሰዎች ለመስበክ የተደረገ ልዩ ዘመቻ
ከ19 አገሮች የተወጣጡ ወንድሞችና እህቶች በኦስትሪያ እና በጀርመን ለሚገኙ የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ለመስጠት ከነሐሴ 31 እስከ ጥቅምት 26, 2019 በተደረገው ዘመቻ ላይ ተካፍለዋል። በዘመቻው የተካፈሉት 1,782 ተሳታፊዎች በድምሩ 40,724 ሰዓት በዚህ የማስተማር ሥራ አሳልፈዋል፤ በተጨማሪም 4,483 ቪዲዮዎችን አሳይተዋል እንዲሁም 24,769 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አበርክተዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞች ወደ ኦስትሪያ እና ጀርመን የገቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ አረብኛ ተናጋሪ ከሆኑ አገሮች የመጡ ናቸው። ከስደተኞቹ መካከል አብዛኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን አጽናኝ መልእክት የመስማት አጋጣሚ አግኝተው አያውቁም። ከካናዳ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የመጡ ወንድሞችና እህቶች በኦስትሪያ እና በጀርመን ውስጥ በአረብኛ ቋንቋ ለሚያገለግሉ 1,108 አስፋፊዎች ድጋፍ ሰጥተዋል። አስፋፊዎቹ እንደ ሃምበርግ፣ ኮሎን፣ ግራትስ፣ ፍራንክፈርትና ቪየና ያሉ ትልልቅ ከተሞችን ጨምሮ በ24 የተለያዩ ቦታዎች አገልግለዋል።
ዘመቻው በተደረገባቸው አገሮች የሚያገለግል አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ዘመቻው ልንጠብቀው ከምንችለው በላይ አዎንታዊ ተጽእኖ አሳድሮብናል። ከሌላ አገር የመጡት ወንድሞች ቅንዓታችን ይበልጥ እንዲቀጣጠል አድርገዋል፤ በመሆኑም ለሰጡን ድጋፍ በጣም አመስጋኞች ነን። በዚህ ልዩ ዘመቻ ላይ የመካፈል መብት በማግኘታችን በጣም ተደስተናል።”
የአረብኛ ቋንቋ ከሚነገርበት አገር የመጣ አንድ ወጣት በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ከተገኘ በኋላ በጣም ተደስቶ አንድን ወንድም “ማሃባ በጀርመንኛ ምን እንደሚባል ታውቃለህ?” ሲል ጠየቀው።
ወንድምም “ሊዪበ (ፍቅር)!” ብሎ መለሰለት።
ወጣቱም እንዲህ አለ፦ “አዎ ልክ ነህ፣ ዛሬ እዚህ በተግባር ያየሁት ይህንን ነው! ደግነት አሳይታችሁኛል። ሁሉም ሰው መጥቶ እየጨበጠ ሰላም ብሎኛል። እዚህ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች እርስ በርስ ሲከባበሩ አይቻለሁ። ሁሉም ሰው እንዲህ ዓይነት ባህርይ ቢያሳይ ዓለማችን ምን ያህል የተለየች ትሆን ነበር!”
አንድ ሌላ ሰው ደግሞ እንዲህ ሲል ስለ ይሖዋ ምሥክሮች አስተያየት ሰጥቷል፦ “ከሰዎች ጋር የመግባባት ልዩ ችሎታ አዳብራችኋል፤ በዓለም ላይ ምርጥ ማኅበረሰብ መሥርታችኋል።”
በጀርመን መኖር ከጀመሩ አንድ ዓመት ገደማ የሆናቸው አረብኛ ቋንቋ ከሚነገርበት አገር የመጡ አንድ ባልና ሚስት ወንድሞችን ቤታቸው ሻይ ጋብዘዋቸው ነበር። ወንድሞች የመጡበትን ዓላማ ከነገሯቸው በኋላ ሚስትየው “የይሖዋ ምሥክሮች ናችሁ?” ብላ ጠየቀቻቸው። ወንድሞች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ሲያረጋግጡላት “የሚገርም ነው! ለወራት ስፈልጋችሁ ነበር። ሌላው ቀርቶ ዋናው ባቡር ጣቢያ ሁሉ ሄጄ ፈልጌያችሁ ነበር። ይኸው አሁን ቤቴ ድረስ መጣችሁልኝ! አምላክ ነው የላካችሁ” አለቻቸው።
በዚህ ልዩ ዘመቻ የተካፈሉ ወንድሞችና እህቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ ሰጪ መልእክት ‘ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሰዎች’ ለማካፈል ያሳዩትን ቅንዓት ይሖዋ በእጅጉ ባርኮታል።—ማቴዎስ 28:19