በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሰርጌ ፊላቶቭ

መጋቢት 2, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በክራይሚያ የተከሰሰው የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር የፍርድ ቤት ብይን እየተጠባበቀ ነው

በክራይሚያ የተከሰሰው የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር የፍርድ ቤት ብይን እየተጠባበቀ ነው

የክራይሚያ ሪፑብሊክ የድዝሃኮይስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ከወንድም ሰርጌ ፊላቶቭ ጋር በተያያዘ መጋቢት 5, 2020 ብይን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ ወንድም ፊላቶቭ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ወኅኒ ቤት ውስጥ የሰባት ዓመት እስር እንዲበየንበት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ወንድም ፊላቶቭ፣ ክራይሚያ ውስጥ በሩሲያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የተከሰሰ የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር ነው።

ቀደም ሲል ሪፖርት እንደተደረገው ወንድም ፊላቶቭ የተያዘው ፖሊሶች ባለፉት ዓመታት ውስጥ በወንድሞቻችን ላይ ካደረጓቸው መጠነ ሰፊ የሆኑ ፍተሻዎች በአንዱ ነው። ጥቅምት 10, 2017 የተወሰኑ ጓደኛሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመወያየትና አብረው መዝሙር ለመዘመር በወንድም ፊላቶቭ ቤት ተሰባስበው ነበር። የሩሲያ ፌደራል ደህንነት ፖሊሶች የድምፅ መቅረጫ መሣሪያ በመጠቀም ያን ስብሰባ በድብቅ ቀድተው ነበር። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ማለትም ኅዳር 15, 2018 ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ፖሊሶች በአካባቢው የሚኖሩ የስምንት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈትሸው ነበር። ከ35 የሚበልጡ የሕግ አስከባሪዎች የወንድም ፊላቶቭን ቤት የፈተሹ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ግማሽ ገደማ የሚሆኑት የታጠቁ የልዩ ኃይል ወታደሮች ነበሩ። ወንድም ፊላቶቭ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ ተለቀቀ።

ወንድም ሰርጌ ፊላቶቭና ባለቤቱ ናታልያ አራት ልጆች አሏቸው፤ ሁለቱ ገና ለአካለ መጠን አልደረሱም። ወንድም ፊላቶቭ የፍርድ ቤት ብይን እየተጠባበቀ ባለበት በዚህ አስጨናቂ ጊዜ እሱና ቤተሰቡ ይሖዋ እንደሚረዳቸው በመተማመን እሱን መጠጊያቸው እንዲያደርጉት እንጸልያለን።—መዝሙር 46:1