በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰኔ 7, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በዓለም ዙሪያ ያሉ ቤቴሎች በድጋሚ መጎብኘት ጀመሩ

በዓለም ዙሪያ ያሉ ቤቴሎች በድጋሚ መጎብኘት ጀመሩ

ሰኔ 1, 2023 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ቤቴሎች በድጋሚ ለጉብኝት ክፍት ሆነዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከሦስት ዓመት በላይ የቤቴል ጉብኝት አልነበረም። በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የቤቴል ቤተሰቦችና ለጉብኝት ለመጡት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይህ ልዩ ቀን ነበር።

አስጎብኚዎች በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለመጎብኘት ለመጡት ሞቅ ያለ አቀባበል ሲያደርጉ

ጎብኚዎቹ በቦታው ሲደርሱ ቤቴላውያን “እንኳን ደህና መጣችሁ!” የሚሉ ምልክቶችን ይዘው፣ መዝሙሮችን እየዘመሩና እያቀፉ በፈገግታ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በወረርሽኙ ወቅት በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት ማገልገል የጀመረው ኤሊስ ቦት እንዲህ ብሏል፦ “ቤቴላውያን ‘እንኳን ደህና መጣችሁ!’ የሚል ምልክት ይዘው በመግቢያው ላይ ቆመው ማየት በጣም የሚያስደስት ነው! ብዙዎች በደስታ ሲያለቅሱ ማየቴ በእርግጥም ቤቴል ልዩ ቦታ መሆኑን እንዳስታውስ አድርጎኛል።” ተመላላሽ ቤቴላዊት ሆና የምታገለግለው አሌክሲስ አሌክሳንደር ለጉብኝት የሚመጡትን መቀበልና ማስተናገድ በመቻሏ በጣም ተደስታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞች ለይሖዋና ለቤቱ ያላቸውን ፍቅር ማየቴ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል።”

ሚ ዮን ጆ እና የስምንት ዓመቱ ልጇ ዩን የኮሪያ ቤቴልን ሲጎበኙ

ሚ ዮን ጆ፣ የስምንት ዓመቱን ልጇን ዩንን በደቡብ ኮሪያ ወደሚገኘው ቤቴል ልትወስደው በመቻሏ በጣም ደስ ብሏታል። ዩን ቤቴልን ለመጎብኘት በጣም ከመጓጓቱ የተነሳ ከጉብኝቱ በፊት ባለው ምሽት እንቅልፍ አልወሰደውም ማለት ይቻላል። ሚ ዮን እንዲህ ብላለች፦ “ልክ ከእንቅልፋችን እንደነቃን ቤቴልን ስለ መጎብኘት የወጣውን የካሌብና የሶፊያን መዝሙር አዳመጥን። ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ስንሄድም መኪና ውስጥ መዝሙሩን እያዳመጥነው ነበር።” ዩን ጉብኝቱን በጣም ከመውደዱ የተነሳ “ቤቴል ውስጥ እንስሳት ቢኖሩ ገነት ይሆን ነበር” በማለት ተናግሯል።

ኖኅ ጆንሰንና ወላጆቹ በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ሲጎበኙ

ኖኅ ጆንሰን የሚኖረው በአልበርታ፣ ካናዳ ሲሆን ስፓይናል መስክዩላር አትሮፊ የሚባል በሽታ አለበት። ኖኅ በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙትን ቤቴሎች ለመጎብኘት በጣም ይመኝ ነበር። የጤናው ሁኔታ በአውሮፕላን ለመጓዝ ስለማይፈቅድለት ወላጆቹ በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲጎበኝ በመኪና 4,100 ኪሎ ሜትር ነድተው ይዘውት ሄዱ። ኖኅ ስለ ጉብኝቱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በጉብኝቱ ወቅት ያየሁት ነገር የፈጠረብኝን ስሜት በአንድ ቃል ብገልጸው “ፍቅር” ነው። የይሖዋንና የወንድሞችን ፍቅር አይቻለሁ።”

ፍዮዶር ዢትኒኮቭ እና ባለቤቱ ዩሊታ በካዛክስታን ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኘውን አውደ ርዕይ ሲጎበኙ

የሰባ ስድስት ዓመቱ ፍዮዶር ዢትኒኮቭ እና ባለቤቱ ዩሊታ፣ በካዛክስታን ቤቴል የሚገኘውን ቤተ መዘክር በመጎብኘታቸው በጣም ተደስተዋል። የቤተ መዘክሩ አንዱ ክፍል ለአሥርተ ዓመታት በታማኝነት የጸኑ ወንድሞችና እህቶችን ፎቶግራፍ ይዟል። ይህ አውደ ርዕይ በተለይ ለፍዮዶር ልዩ ስሜት ፈጥሮበታል፤ ምክንያቱም ከአብዛኞቹ ጋር አብሮ አገልግሏል። ፍዮዶር ይህን አውደ ርዕይ ለማዘጋጀት ለተደረገው ጥረት ያለውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች የአገልግሎት ታሪካችንን ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት ጠብቀው ማቆየት ከቻሉ ይሖዋማ ሁሉንም ነገር በደንብ ያስታውሳል፤ እያንዳንዳችን ያከናወንነውንም ሥራ ይበልጥ ያደንቃል።”

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቤቴሎችን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶችን በድጋሚ መቀበል በመቻላችን በጣም ተደስተናል። በቀጣዮቹ ቀናትም ለሚመጡት በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች አቀባበል ለማድረግ ጓጉተናል!—መዝሙር 122:1

ከታች ባሉት ፎቶግራፎች ላይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተለያዩ ቤቴሎችንና ቤተ መዘክሮችን ሲጎበኙ ይታያል።

 

አርጀንቲና

ቤልጅየም

ብራዚል

ዶሚኒካን ሪፑብሊክ

ኢኳዶር

ፈረንሳይ

ካዛክስታን

ኒው ካሊዶኒያ

ናይጄሪያ

ደቡብ ኮሪያ

ዩናይትድ ስቴትስ—ዎልኪል፣ ኒው ዮርክ

ዩናይትድ ስቴትስ—ዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ