መጋቢት 26, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በወረርሽኙ መሃል አዳዲስ የስብከት ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ነው
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። የይሖዋ ምሥክሮች የባለሥልጣናትን ትእዛዝ እያከበሩ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴያቸውን ማከናወን ይፈልጋሉ። ወረርሽኙ በተስፋፋባቸው ክልሎች ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች አገልግሎታቸውን ለማከናወን አዳዲስ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ነው።
በፒዛ፣ ጣሊያን የሚኖር አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አገልግሎታችን በጣም አስደሳች ሆኗል! ብዙ ሰዎች ቤታቸው ስለሚገኙ እኔና ባለቤቴ ስልካችን ውስጥ ያሉትን አድራሻዎች በማየት ከሰዎች ጋር በቪዲዮ ጥሪ አማካኝነት ለመነጋገር ሞከርን። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችና ተመላልሶ መጠየቆች አግኝተናል፤ አንዳንዶቹ አዲሶች ናቸው፤ ሌሎቹን ደግሞ ከዚህ በፊት አነጋግረናቸው እናውቃለን። በመሆኑም በአገልግሎት ብዙ ሰዓት ማሳለፍና ግሩም ውጤት ማግኘት ችለናል።”
በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ አስፋፊዎች በወረርሽኙ የተነሳ የjw.orgን እና የJW ላይብረሪን አንዳንድ ገጽታዎች ይበልጥ ለመጠቀም ተነሳስተዋል። ለምሳሌ አንድ ወንድም ከቀድሞ ጥናቱ የጽሑፍ መልእክት ደረሰው፤ ይህ ሰው ጥናት ያቆመው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር። ጥናቱ ይህ ወረርሽኝ ስለ መጨረሻው ዘመን ምልክቶች እንዲያስብ እንዳደረገው ለወንድም ገለጸለት። ወንድምም በJW ላይብረሪ ላይ የሚገኘውን “ሊንክ አጋራ” የሚለውን ገጽታ በመጠቀም ለቀድሞ ጥናቱ ጠቃሚ ርዕሶችን በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት ላከለት። ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የመጨረሻው ዘመን ምልክት የሆነው ይህ ክንውን የብዙ ሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳነቃቃ ማየታችን አበረታቶናል።”
በመላው ዓለም ከሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የደረሱን ሪፖርቶች ወንድሞችና እህቶች ለአገልግሎታቸው ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ያሳያሉ። ወንድሞቻችን “ማስተዋል የታከለበት ጥበብ” ተጠቅመው ምሥራቹን መስበካቸውን እንደቀጠሉ ማየታችን በጣም ያስደስተናል።—ሚክያስ 6:9 የግርጌ ማስታወሻ
በፖርቶ ሪኮ የሚያገለግል የወረዳ የበላይ ተመልካች የስምሪት ስብሰባ ሲመራ
በጀርመን የሚኖሩ አቅኚዎች በቪዲዮ እየተነጋገሩ አብረው ደብዳቤ ሲጽፉ
ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመራ
በፈረንሳይ የሚኖሩ ባልና ሚስት በስልክ ሲመሠክሩ
በሃዋይ የምትኖር እህት ከልጇ ጋር ደብዳቤ ስትጽፍ