በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የጊልያድ ተመራቂዎች ፕሮግራሙን ለሚከታተሉ ወንድሞችና እህቶች እጃቸውን በማውለብለብ ሰላምታ ሲሰጡ

መጋቢት 20, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጊልያድ ምረቃ ፕሮግራም

በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጊልያድ ምረቃ ፕሮግራም

ከብዙ ነገሮች አንጻር ሲታይ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 148ኛ ክፍል የተማሪዎች ምረቃ ከዚያ በፊት ከነበሩት የምረቃ ፕሮግራሞች ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ ሆኖም አንድ መሠረታዊ ልዩነት ነበረው፤ በአዳራሹ ውስጥ ምንም ተመልካች አልነበረም። ሁሉም ተመልካቾች ፕሮግራሙን በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት አማካኝነት እንዲከታተሉ ተደርጓል። ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ በተከሰተበት በዚህ ወቅት የተከናወነው ይህ መንፈሳዊ ፕሮግራም ድርጅቱ ከሁኔታዎች ለውጥ ጋር ራሱን እንደሚያስማማ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው።

የምረቃ ፕሮግራሙ በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትምህርት ማዕከል ውስጥ የተካሄደው መጋቢት 14, 2020 ነበር። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር ነበር። በፕሮግራሙ ላይ 55 ተማሪዎች ተመርቀዋል። a

ከምረቃው በፊት በነበሩት ጥቂት ሳምንታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር። ከዚህ በፊት jw.org ላይ በወጣ ዜና ላይ እንደተገለጸው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ሁኔታውን ሲከታተል እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሚሰጡት ማሳሰቢያ ጋር የሚስማማ መመሪያ ለሁሉም ጉባኤዎች ሲያስተላልፍ ቆይቷል።

ባለሥልጣናቱ ካወጧቸው መመሪያዎች መካከል አንዱ በርከት ያሉ ሰዎች አንድ ላይ እንዳይሰበሰቡ ይከለክላል። በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ የበላይ አካሉ በፕሮግራሙ ላይ ከውጭ የተጋበዙ እንግዶች እንዳይገኙ ወሰነ። በተጨማሪም በአዳራሹ ውስጥ ተመልካቾች እንዳይኖሩ ተደረገ። የቤቴል ቤተሰብና የጊልያድ ተማሪዎች ይህን መመሪያ በመደገፍ ጥሩ ምሳሌ ትተዋል።—ዮሐንስ 13:34, 35

ይሁንና የጊልያድ ተማሪዎች የጋበዟቸው እንግዶችና የቤቴል ቤተሰቡ በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት አማካኝነት ፕሮግራሙን እንዲከታተሉ ዝግጅት ተደረገ። ይህ ዝግጅት የተመራቂዎቹን ጓደኞችና ቤተሰቦች ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ10,000 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ፕሮግራሙን በቀጥታ እንዲከታተሉ አስችሏል።

የበላይ አካሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባለበት በዚህ ጊዜም መንፈሳዊ ፕሮግራሞች፣ በተለይም ሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች ቋሚ የአምልኳችን ክፍል ሆነው እንዲቀጥሉ ይፈልጋል። በመሆኑም የበላይ አካሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የአካባቢያቸውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ ዝርዝር መመሪያዎችን ሰጥቷል። ይህም አስፋፊዎች በትናንሽ ቡድኖች ሆነው ወይም እንደ ቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ ያሉ አማራጮችን ተጠቅመው እንዲሰበሰቡ ማድረግን ይጨምራል። ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ለሁሉም ጉባኤዎች ከሚቀርበው ያልተቋረጠ መንፈሳዊ ምግብ ተጠቃሚ እንደሚሆን እንተማመናለን።

ድርጅታችን በይሖዋ ኃይል ማንኛውንም አስቸጋሪ ሁኔታ መወጣት እንደሚችል እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 18:29

a የ148ኛው የጊልያድ ምረቃ ሙሉ ፕሮግራም ሰኔ 2020 jw.org ላይ ይወጣል።