ግንቦት 3, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና
“ትኩረታችሁ ምንጊዜም ከይሖዋ ጋር ባላችሁ ዝምድና ላይ ይሁን”
በዩክሬንና በፖላንድ ያሉ ወንድሞችን ያበረታታ ልዩ ፕሮግራም
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተጎዱ ወንድሞችንና እህቶችን በመንፈሳዊ ለማበረታታት ሚያዝያ 26, 2022 ወደ ፖላንድ ሄደ።
በፖላንድ እና በዩክሬን የሚገኙ ጉባኤዎች በሙሉ ሚያዝያ 30, 2022 በተደረገው ልዩ ፕሮግራም ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር። ከዩክሬን የመጡ ስደተኞች እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሠራተኞች በዋርሶ፣ ፖላንድ በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ ላይ በአካል ተገኝተዋል። በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተገኙትን ጨምሮ በፖላንድና በዩክሬን የሚገኙ ከ250,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
ወንድም ሳንደርሰን በፕሮግራሙ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ስለ እናንተ ያስባሉ፣ ይጸልያሉም። በዋናው ቢሮ በየቀኑ በሚቀርቡ ጸሎቶች ላይ በሩሲያና በዩክሬን የሚኖሩ ወንድሞች ይጠቀሳሉ፤ የበላይ አካሉ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይም ይነሳሉ።” ወንድም ሳንደርሰን ተሰብሳቢዎቹን እንደሚከተለው በማለት አበረታቷቸዋል፦ “አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጠሟችሁ ማለት በይሖዋ ፊት ተቀባይነት አጥታችኋል ማለት አይደለም። ይሖዋ ያያችኋል፤ ይወዳችኋል፤ በተለይ ደግሞ ለተጨነቁ ሰዎች ቅርብ ነው።”
ወንድም ሳንደርሰን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ትኩረታችሁ ምንጊዜም ከይሖዋ ጋር ባላችሁ ዝምድና ላይ ይሁን። ግባችን እንዲሁ በሕይወት መትረፍ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናዎቹ እምነታችንን እንዲያጠናክሩትና ወደ ይሖዋ ይበልጥ የሚያቀርቡን እንዲሆኑ እንፈልጋለን። ይሖዋም ሊያስተምረን የሚፈልገው ይሄንኑ ነው።”
በኦዴሳ፣ ዩክሬን የሚኖር ሴርሂ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ባደረብኝ ጭንቀት፣ ሐዘንና ፍርሃት የተነሳ ባለፉት ሳምንታት ጥሩ እንቅልፍ አልተኛሁም ነበር። ይሁንና [ልዩ ፕሮግራሙ] ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚንከባከብ አልፎ ተርፎም በግለሰብ ደረጃ ስለ እያንዳንዳችን እንደሚያስብ ያለኝን እምነት አጠናክሮልኛል።”
ከኪየቭ፣ ዩክሬን የተሰደደች ታትያና የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ለእኔ ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ ዛሬ ማስተዋል ችያለሁ። ይሖዋ እቅፍ እንዳደረገኝ ተሰምቶኛል፤ ፍቅሩንም ማጣጣም ችያለሁ። የትም ብንሆን ይሖዋ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው።”
ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከልብ እንወዳቸዋለን፤ ልዩ ፕሮግራሙ ይሖዋ ለሕዝቡ ‘ታማኝ ፍቅር’ እንደሚያሳይ እንዲተማመኑ እንደሚያደርጋቸው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 136:1