ጥቅምት 1, 2019
ዓለም አቀፋዊ ዜና
ንቁ! መጽሔት መቶ ዓመት አስቆጠረ
ጥቅምት 1, 2019 ንቁ! መጽሔት 100 ዓመት ሞላው። ይህ መጽሔት በ211 ቋንቋዎች የሚተረጎም ሲሆን በየዓመቱ ከ280 ሚሊዮን የሚበልጡ ቅጂዎች ይታተማሉ፤ በመሆኑም ከመጠበቂያ ግንብ ቀጥሎ በሚተረጎምባቸው ቋንቋዎች ብዛትና በስርጭቱ ረገድ በዓለም ላይ ሁለተኛውን ቦታ ይዟል።
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ኸርድ እንዲህ ብሏል፦ “ንቁ! የሚዳስሳቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርገዋል። ባለፉት ዓመታት የዚህ መጽሔት ገጽታም ሆነ አቀራረብ ቢቀያየርም በስብከቱ ሥራችን የምንጠቀምበት ውጤታማ መሣሪያ ሆኖ ቀጥሏል። መጽሔቱ አንድ መቶ ዓመት ማስቆጠሩ በጣም አስደሳች ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሥራው በአምላክ መንፈስ እንደሚሠራ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።”
መስከረም 1919 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደው ጉልህ ቦታ የሚሰጠው ትልቅ ስብሰባ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ወርቃማው ዘመን (የንቁ! መጽሔት የመጀመሪያ ስያሜ) የተሰኘው መጽሔት መውጣቱን አስታውቀው ነበር። በ1937 የመጽሔቱ ስያሜ ተቀይሮ መጽናኛ ተባለ፤ እንዲህ የተደረገው በወቅቱ ብዙ ሰዎች መጽናኛ ያስፈልጋቸው ስለነበር ነው። በመጨረሻም በ1946 መጽሔቱ ንቁ! ተባለ፤ ምክንያቱም የመጽሔቱ ዓላማ፣ አንባቢዎች የምንኖርበት ዘመን ያለውን መንፈሳዊ ትርጉም እንዲያስተውሉ መርዳት ነው።
ይህ መጽሔት ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ በመብቃቱ የተሰማንን ደስታ እየገለጽን ወደፊትም ቢሆን ‘ምሥራቹን በተሟላ ሁኔታ ለመመሥከር’ በምናከናውነው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማሩ ሥራ በንቁ! መጽሔት መጠቀማችንን እንቀጥላለን።—የሐዋርያት ሥራ 20:24