መጋቢት 31, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
አረጋውያን በወረርሽኙ መሃል ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዲቀጥሉ መርዳት
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአረጋውያን ላይ ሊያስከትል ከሚችለው አስከፊ አደጋ አንጻር በዕድሜ የገፉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የጤና ባለሙያዎችን ምክር በመከተል ከቤታቸው ላለመውጣት ወስነዋል። ሆኖም ብቸኛ አልሆኑም ወይም ሥራ ፈተው አልተቀመጡም። በስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በአገልግሎት ለመካፈል የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እየተጠቀሙ ነው።
በሮም፣ ጣሊያን የሚኖሩ በ1952 የተጠመቁ አንዲት የ94 ዓመት አረጋዊት እህት ወረርሽኙ ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን ከቤት መውጣት አይችሉም ነበር። እኚህ እህት የተቀዱ ስብሰባዎችን በJW ስትሪም አማካኝነት ይከታተሉ የነበረ ቢሆንም በራሳቸው ጉባኤ ስብሰባ ላይ ከተገኙ ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል። አሁን ግን ሽማግሌዎች በቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ አማካኝነት የጉባኤ ስብሰባ እንዲደረግ ስለወሰኑ እሳቸውም የራሳቸውን ጉባኤ ስብሰባ መከታተልና በጉባኤያቸው ያሉትን ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ማየት ችለዋል።
በስፓኒሽ ፎርክ፣ ዩታ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ስቴፈኒ አይትከን የተባሉ መስማት የተሳናቸው እህት የሚኖሩት በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ ነው፤ ተቋሙ አረጋውያኑን ማንም ሰው መጥቶ እንዳይጠይቅ ከልክሏል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ባለቤቱ እኚህ እህት ቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ ማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም እንዲጭኑ ረዷቸው፤ እንዲህ ያደረጉት በተቋሙ የመስታወት በር በኩል ለእህት በምልክት ቋንቋ መመሪያ በመስጠት ነው። እህት አይትከን ፕሮግራሙን ከጫኑ በኋላ ታብሌታቸውን እቅፍ አደረጉት። ከጉባኤያቸው ጋር መገናኘት በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል።
አረጋውያንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሁን ባለው ወረርሽኝ የተነሳ የመጡትን ለውጦች ለማስተናገድ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀማቸው ይሖዋ ሕዝቦቹ “የብሔራትን ወተት” እንደሚጠጡ የገባውን ቃል ያስታውሰናል። (ኢሳይያስ 60:16) ይሖዋ በዚህ አስጨናቂ ወቅት በምድር ያሉ አገልጋዮቹን ለመርዳት ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን እናውቃለን።
በስዊድን የሚኖሩ ባልና ሚስት (ከላይ በስተ ግራ)፣ በፈረንሳይ የሚኖሩ ወንድም (ከታች በስተ ግራ) እና በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ ባልና ሚስት (በስተ ቀኝ) በጉባኤ ስብሰባ ሲካፈሉ
በኖርዌይ የሚኖሩ ባልና ሚስት በስልክ ሲመሠክሩ
በጣሊያን የሚኖሩ ባልና ሚስት እረኝነት ሲደረግላቸው