በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 23, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

አራቱ ወንጌሎች በኦካን ቋንቋ ወጡ

አራቱ ወንጌሎች በኦካን ቋንቋ ወጡ

ነሐሴ 13, 2023 የሱሪናም ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሮይ ዚማን የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች በኦካን ቋንቋ መውጣታቸውን አስታውቋል። በፓራማሪቦ፣ ሱሪናም በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በተካሄደው ልዩ ፕሮግራም ላይ 2,713 ሰዎች በአካል ተገኝተዋል። የፍሬንች ጊያና ከተማ በሆነችው በካዬን ባለው የስብሰባ አዳራሽና በሌሎች ቦታዎች የነበሩ 691 ሰዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት ተከታትለዋል። የአራቱንም ወንጌሎች የኤሌክትሮኒክ ቅጂ በዚያኑ ዕለት ማውረድ የተቻለ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል ደግሞ በሕትመት ተዘጋጅቶ ቀርቧል። የቀሩት ሦስቱ ወንጌሎች በታተመ ቅጂ የሚወጡት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በኦካን ቋንቋ ሲዘጋጅ ነው።

ኦካን ከተለያዩ ቋንቋዎች የተወራረሰ ቋንቋ ሲሆን አብዛኞቹ የቋንቋው ተናጋሪዎች የሚገኙት በሱሪናም እንዲሁም በአጎራባቿ በፍሬንች ጊያና ነው። በዚህ ቋንቋ የተዘጋጁ የሕትመት ውጤቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው። በኦካን ቋንቋ በሚመሩ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች ለስብሰባዎችና ለአገልግሎት እየተጠቀሙ የሚገኙት በስራናንቶንጎ ቋንቋ የተዘጋጀውን አዲስ ዓለም ትርጉም ነው። ስራናንቶንጎ በሱሪናም በስፋት የሚነገር ቋንቋ ቢሆንም ብዙዎቹ የኦካን ቋንቋ ተናጋሪዎች ግን በደንብ አይችሉትም። ስለዚህ አስፋፊዎቹ ሲያገለግሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ወደ ኦካን ቋንቋ ለመተርጎም ይገደዳሉ። በትርጉም ሥራው የተሳተፈ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ትርጉም በመውጣቱ በጣም ተደስተናል። ምክንያቱም በየትኛውም ዕድሜና የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ የኦካን ቋንቋ ተናጋሪዎች ከአምላክ ቃል ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ ያስችላል።”

እኛም ሆንን የኦካን ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መዘጋጀቱ ቀና ልብ ያላቸው ተጨማሪ ሰዎች ይሖዋን እንዲያወድሱት እንደሚያነሳሳቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 34:1