በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የፓተርሰን የጎብኚዎች ማዕከል። ውስጠኞቹ ፎቶግራፎች፦ ጎብኚዎች “የመጀመሪያው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ መንደር” በተባለው አሳታፊ ጉብኝት ሲካፈሉ

ጥር 26, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና

አሳታፊና በዓይነቱ ልዩ የሆነው አዲሱ የፓተርሰን የጎብኚዎች ማዕከል

አሳታፊና በዓይነቱ ልዩ የሆነው አዲሱ የፓተርሰን የጎብኚዎች ማዕከል

በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል የተገነባው አዲሱ የፓተርሰን የጎብኚዎች ማዕከል ከጥር 1, 2024 ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል። ከማዕከሉ ልዩ ገጽታዎች መካከል አንዱ “የመጀመሪያው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ መንደር” የተባለው ሙዚየም ነው። በቤቴል በሙዚየም ዲፓርትመንት ውስጥ የሚያገለግለው ወንድም አይዛያ ሚለር እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ መንደሩ የተሠራው ጎብኚዎች ያ ዘመን ሕያው እንዲሆንላቸውና ትምህርት እንዲቀስሙበት በሚያስችል መንገድ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንዲህ ያለው አሳታፊ የሆነ የትምህርት ዘዴ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በእጅጉ ይጠቅማል።” አንዲት ጎብኚ ከጉብኝቱ በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ሙዚየም ወደ ኋላ ተጉዤ በጥንቷ የእስራኤል ምድር ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጓል። በጣም ልዩ ነው!”

ሙዚየሙ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በእስራኤላውያን መንደር ውስጥ የነበሩትን እንስሳት፣ ምግቦች፣ አትክልት እንዲሁም የነዋሪዎቹን የዕለት ተዕለት ሕይወት ሕያው በሆነ መንገድ ያሳያል። ለምሳሌ በሙዚየሙ ውስጥ ያሉት የወይራ ዛፎች፣ በእስራኤል ያሉትን የወይራ ዛፎች ቅርጽ በመከተል በእጅ የተሠሩ ናቸው። ጎብኚዎች ወፍጮ ተጠቅመው እህል መፍጨት እንዲሁም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ይጓዙበት የነበረው ዓይነት የዓሣ ማጥመጃ ጀልባ ላይ መውጣት ይችላሉ። አንድ ወንድም እንዲህ በማለት በደስታ ተናግሯል፦ “ኢየሱስ ባሕሩን ‘ጸጥ በል! ረጭ በል!’ ያለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ክፍል እንደሆንኩ ተሰምቶኛል።” (ማርቆስ 4:39) ጎብኚዎች በጥንት ዘመን የነበሩትን ምኩራቦች ንድፍ በመከተል የተሠራውን ምኩራብ ሲጎበኙ የአምላክ ቃል ጮክ ተብሎ ሲነበብ በቦታው ቁጭ ብለው በጥሞና እያዳመጡ እንዳሉ አድርገው በዓይነ ሕሊናቸው መሣል ይችላሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መንደሩን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች (ከላይ በስተ ግራ ጀምሮ ዙሪያውን)፦ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የዓሣ ማጥመጃ ጀልባ፣ ወፍጮ፣ ምኩራብ እና የገበያ ቦታ

ሬቤካ እና ማርኮስ በመጽሐፍ ቅዱስ መንደሩ ዱካ የሚሠራው እንዴት እንደሆነ ሲማሩ

ሙዚየሙ ያለው ሌላው ልዩ ገጽታ፣ ጎብኚዎች በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ነዋሪዎችን ገጸ ባሕርይ ወክለው የሚተውኑ ወንድሞችንና እህቶችን በማነጋገር በዚያ ዘመን ስለነበረው ሕይወት መማር የሚችሉበት አጋጣሚ መስጠቱ ነው። ጎብኚዎች በኢየሱስ ዘመን የተለመዱ በነበሩ አንዳንድ ሥራዎች የመሳተፍ አጋጣሚም አላቸው። ማርኮስ የተባለ የአሥር ዓመት ልጅ “እስራኤላዊው አናጢ ዱካ እንዲሠራ ያገዝኩበትን የጉብኝቱን ክፍል በጣም ወድጄዋለሁ!” ብሏል። የስምንት ዓመቷ ሬቤካም “እኔም የወደድኩት እሱን ክፍል ነው፤ ወፍጮ ተጠቅመን ስንዴ የፈጨንበትንም ክፍል ወድጄዋለሁ” ብላለች።

የጎብኚዎች ማዕከሉ ከዚህኛው ሙዚየም በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ክፍሎች አሉት። “የመጀመሪያው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ሳንቲሞች” የተባለው ክፍል በቀላሉ የማይገኘውን ቴትራድራክማ የተባለውን ሳንቲም ጨምሮ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የተለያዩ ሳንቲሞችን ያሳያል። “ልጆችሽ ሁሉ ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ” የሚል መጠሪያ ያለው ሙዚየም ደግሞ ጎብኚዎች የይሖዋ ድርጅት ስላዘጋጃቸው የተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች እንዲያውቁና መለኮታዊ ትምህርት ስለሚያስገኘው ጥቅም እንዲያስተውሉ ይረዳል። በተጨማሪም “ለምሥራቹ መሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ” የተባለው ሙዚየም ስደት ያጋጠማቸውን በተለያዩ አገሮች ያሉ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ምሳሌ እንዲሁም የይሖዋ ድርጅት እንዴት በታማኝነት ድጋፍ እንዳደረገላቸው ያሳያል።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ “የመጀመሪያው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ሳንቲሞች” የተባለው ሙዚየም፣ “ልጆችሽ ሁሉ ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ” የተባለው ሙዚየም እና “ለምሥራቹ መሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ” የተባለው ሙዚየም

በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ የፓተርሰንን የጎብኚዎች ማዕከል በመጎብኘት በዚያ የተዘጋጀላቸውን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ስጦታ እንዲያዩ ተጋብዘዋል። ይህ የጎብኚዎች ማዕከል ይሖዋ ሕዝቡን ምን ያህል እንደሚወድና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የሚያሳይ ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።​—ያዕቆብ 1:17