በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 12, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና

አዲስ ዓለም ትርጉም በሦስት ተጨማሪ ቋንቋዎች በብሬይል ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም በሦስት ተጨማሪ ቋንቋዎች በብሬይል ወጣ

ባለፉት ጥቂት ወራት አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሦስት ቋንቋዎች ማለትም በጀርመንኛ፣ በኮሪያኛና በዩክሬንኛ በብሬይል ወጣ። ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎቹ jw.org ላይ ወጥተዋል። በኮሪያኛና በዩክሬንኛ የተዘጋጁትን የብሬይል ፋይሎች ኖትቴከር በተባሉ ተንቀሳቃሽ የብሬይል መጻፊያ ማሽኖች ማንበብ ይቻላል። የጀርመንኛውን የብሬይል ፋይል ደግሞ በስክሪን ማንበቢያ አማካኝነት ማስነበብ ይቻላል።

አንድ ኮሪያዊ ወንድም ኖትቴከር ተጠቅሞ ኤሌክትሮኒክ የብሬይል ፋይል ሲያነብ

ዓይነ ስውራን በድምፅ የተቀዱ ጽሑፎችንና ኖትቴከሮችን የሚጠቀሙ ቢሆንም ብዙዎቹ የታተሙ የብሬይል ጽሑፎችን ማንበብ ይመርጣሉ። በጀርመንኛ ብሬይል የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ጥራዞች ታትመው ለአስፋፊዎች ተልከዋል። በኮሪያኛ ብሬይል የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ በመጪዎቹ ወራት ታትሞ ለአስፋፊዎች ይላካል። በዩክሬንኛ ብሬይል የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ግን በጦርነቱ ምክንያት መቼ የአስፋፊዎች እጅ እንደሚገባ አልታወቀም።

መጽሐፍ ቅዱስን በብሬይል ለማዘጋጀት በአዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ያሉትን በርካታ ማመሣከሪያ ጽሑፎች ጨምሮ ቃላቱን ወደ ብሬይል ፊደላት መገልበጥ ይጠይቃል። ካርታዎችና ሥዕላዊ መግለጫዎች ለዓይነ ስውራን ወደሚገባ ፎርማት መለወጥ አለባቸው።

በጀርመን የምትኖር አንዲት ዓይነ ስውር እህት እንዲህ ብላለች፦ “በብሬይል ያነበብኩትን ነገር አልረሳውም። ከማዳመጥ በጣም የተሻለ ነው። ለይሖዋ ያለኝን አድናቆትና በእሱ ላይ ያለኝን እምነት አጠናክሮታል።”

ከላይ በስተ ግራ፦ የብሬይል ነጠብጣቦችን ለየት ባለ ወረቀት ላይ የሚቀርጸው ማሽን። መሃል፦ አንዲት እህት የብሬይል መጽሐፍ ቅዱስ ስትጠርዝ። በስተ ቀኝ፦ ወደ ዓይነ ስውራን አስፋፊዎች የሚላኩ የብሬይል ጥራዞች ሲዘጋጁ

ሁሉም የብሬይል መጽሐፍ ቅዱሶች የሚታተሙት ዎልኪል፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው። የብሬይል ጽሑፎችን ለማተም የሚያገለግለው ማሽን የብሬይል ነጠብጣቦችን ለየት ባለ ወረቀት ላይ ይቀርጻቸዋል፤ ከዚያም ወረቀቶቹ ተሰብስበው ይጠረዛሉ፤ ጥራዞቹም ወደ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ተልከው ለአስፋፊዎች ይሰራጫሉ። በብሬይል የተዘጋጀው ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም ከ30 ጥራዝ በላይ ሊሆንና መደርደሪያ ላይ እስከ ሁለት ሜትር የሚደርስ ቦታ ሊይዝ ይችላል።

የኮሪያኛውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ብሬይል በመገልበጡ ሥራ የተካፈለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ዓይነ ስውር የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ከዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያገኙትን መንፈሳዊ ጥቅምና ማጽናኛ ስናስብ ለይሖዋ አምላክ ያለን አድናቆት ይጨምራል።”

በብሬይል የተዘጋጁት እነዚህ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶች ዓይነ ስውር የሆኑ ወንድሞችንና እህቶችን እንደሚጠቅሟቸው እርግጠኞች ነን። በእርግጥም ይሖዋ “በመልካም ነገሮች” አጥግቧቸዋል።—መዝሙር 107:9