በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 1, 2021 የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሳይቤሪያ በባቡር የተጋዙበትን 70ኛ ዓመት ለማሰብ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቶ ነበር

ሚያዝያ 30, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና

አጠቃላይ ዜና | ወደ ሳይቤሪያ በግዞት የተወሰዱትን የይሖዋ ምሥክሮች 70ኛ ዓመት ለማሰብ በሞልዶቫ፣ በሩሲያ እና በዩክሬን የተለያዩ ኮንፈረንሶች ተካሄዱ

አጠቃላይ ዜና | ወደ ሳይቤሪያ በግዞት የተወሰዱትን የይሖዋ ምሥክሮች 70ኛ ዓመት ለማሰብ በሞልዶቫ፣ በሩሲያ እና በዩክሬን የተለያዩ ኮንፈረንሶች ተካሄዱ

በሶቪየት አገዛዝ ሥር የነበሩ 9,793 የይሖዋ ምሥክሮች በ1951 ወደ ሳይቤሪያ የተጋዙበትን ኦፐሬሽን ኖርዝ የተባለ ዘመቻ 70ኛ ዓመት ለማሰብ በሞልዶቫ፣ በሩሲያ እና በዩክሬን የተለያዩ ኮንፈረንሶች ተካሂደዋል፤ የኮንፈረንሶቹ ዓላማ እውቀት ማስጨበጥና ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ መስጠት ነበር።

በአንዳንዶቹ ኮንፈረንሶች ላይ ተሰብሳቢዎች ስለ ኦፐሬሽን ኖርዝ ለማሳወቅ ተብሎ የተዘጋጀውን 1951deport.org የተባለ ድረ ገጽ እንዲጎበኙ ግብዣ ቀርቦላቸዋል። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ይህ ድረ ገጽ በሩሲያኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በዩክሬንኛ ይገኛል። ድረ ገጹ ስለ ዘመቻው ሰፊ የሆነ ታሪካዊ መረጃ እና ማብራሪያ ይሰጣል።

ሚያዝያ 1 | የሞልዶቫ እውቀት ማስጨበጫ ኮንፈረንስ

በቦልቲ ባለው አሌኩ ሩሶ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ሊዲያ ፓዱሪያክ እንዲህ ብለዋል፦ “የሶቪየት ኅብረት በ1951 የግዞት ዘመቻውን ያካሄደው ከኮሚኒዝም ውጭ ሌላ ጽንሰ ሐሳብ የሚያራምዱ ሰዎች ምን እንደሚጠብቃቸው ለሰዎች ለማሳየት ነው።”

ሚያዝያ 1, 2021 ወንድም ቪክቶር ዶርኒቼንኮ (ከላይ በስተግራ) በሞልዶቫ ያሉ ሦስት የትምህርት ተቋማት ባዘጋጁትና በኢንተርኔት አማካኝነት በተደረገው ኮንፈረንስ ላይ ንግግር ሲያቀርብ

ሆኖም ኢንስቲትዩት ኦቭ ሂስትሪ የተባለው ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ኒኮላይ ፉስቴ እንደተናገሩት “ኦፐሬሽን ኖርዝ ግቡን ማሳካት አልቻለም። . . . የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት አልጠፋም፤ ተከታዮቹም ቢሆኑ እምነታቸውን ማስፋፋታቸውን አላቆሙም። እንዲያውም ከቀድሞው በበለጠ ድፍረት መስበካቸውን ቀጥለዋል።”

ኢንስቲትዩት ኦቭ ሂስትሪ በተባለው ተቋም ውስጥ ተመራማሪና የኮንፈረንሱ ሊቀ መንበር የሆኑት ዶክተር ቨርጂሉ በርላዲያኑ፣ በግዞት ተወስደው ለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። በእነዚህ ሰዎች ላይ ስላስተዋሉት አስደናቂ ባሕርይ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “በፊታቸው ላይ የሚነበበው ሰላም በጣም ያስገርማል፤ የሶቪየት አገዛዝ ከፍተኛ ጭቆና ቢያደርስባቸውም የጥላቻ ስሜት አላደረባቸውም።”

በሞልዶቫ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግለው ወንድም ቪክቶር ዶርኒቼንኮ በሶቪየት አገዛዝ ሥር የነበረው ጭቆና በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ውስጥ እየተደገመ ያለው እንዴት እንደሆነ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “የሚያሳዝነው፣ ታሪክ ራሱን እየደገመ ነው። በ2017 የበጋ ወራት፣ በሩሲያ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲሁም በውስጡ ያሉት 175,000 የይሖዋ ምሥክሮች ያለምንም ሕጋዊ መሠረት እገዳ ተጥሎባቸዋል። ሰዎች ለይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ጭፍን ጥላቻና እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ የሚናፈሰው የተሳሳተ መረጃ የእነዚህ ሰዎች የማሰብ፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ መሠረታዊ የሆኑ መብቶቻቸው እንዲገፈፉ ምክንያት ሆኗል።”

ሚያዝያ 1 | የሞስኮ ጋዜጣዊ መግለጫ

ቀደም ሲል ሪፖርት እንዳደረግነው አምስት ምሁራንና የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች እንዲሁም የአውሮፓ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ተወካይ የሆነው ወንድም ያሮስላቭ ሲቩልስኪ ስለ ኦፐሬሽን ኖርዝ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሩሲያ ስላለው ሁኔታ ተናግረዋል። ሙሉው ኮንፈረንስ በሩሲያኛ እና በእንግሊዝኛ በኢንተርኔት በቀጥታ ተላልፏል።

ሚያዝያ 6 | በሞስኮ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የመታሰቢያ ማኅበር ያዘጋጀው የእውቀት ማስጨበጫ ውይይት

ቀደም ሲል ሪፖርት እንዳደረግነው ይህ ፕሮግራም በሩሲያኛ ብቻ በኢንተርኔት በቀጥታ ተላልፏል።

ሚያዝያ 8 | በኪየቭ የተደረገው የእውቀት ማስጨበጫ ኮንፈረንስ

ከስድስት አገራት የተውጣጡ 14 ምሁራን እንዲሁም በዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግለው ወንድም ኢቫን ሪሄር አጫጭር ንግግር አቅርበዋል። አንዳንድ ምሁራን በሚያደርጉት ምርምር እንዲያግዛቸው፣ በግዞት ከተወሰዱት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከተወሰኑት ጋር ሰፊ ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። ተመልካቾች ከእነዚህ ቃለ መጠይቆች ላይ ተቀንጭበው የተወሰዱ ቪዲዮዎችን እንዲመለከቱ ተደርጓል።

በፖላንድ በሚገኘው የሲሌዢያ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ሳይንስ ተቋም ውስጥ የታሪክ ምሁር እና ተመራማሪ ሆነው የሚሠሩት ዶክተር ቶማሽ ቡጋይ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩና ይሠሩ የነበረ ቢሆንም የሚመሩባቸውን የሥነ ምግባር ደንቦችም ሆነ ሃይማኖታዊ አቋማቸውን አላላሉም። የተሻለ ሥራ፣ የኑሮ ሁኔታ ወይም ምግብ ለማግኘት ሲሉ ሐሳባቸውን በትንሹም ቢሆን ለመቀየር ፈቃደኛ አልሆኑም።” ዶክተር ቡጋይ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ከአቋማቸው ፍንክች አለማለታቸው “ልዩ ሰዎች” እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።

የዩክሬን ሃይማኖታዊ ጥናት ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ልዩድሚላ ፊሊፖቪች በዩክሬን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በ36 ቋንቋዎች እንደሚያሰራጩ ገልጸዋል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎት እነሱን ብቻ ሳይሆን መላውን ማኅበረሰብ የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ ጎላ አድርገው ተናግረዋል። “የይሖዋ ምሥክሮች የዩክሬን ዜጎች ለሚያጋጥሟቸው በርካታ ማኅበራዊ ችግሮች መፍትሔ ይሰጣሉ” ብለዋል። ዓይነ ስውር ለሆኑና መስማት ለተሳናቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር እንዲሁም እነዚህ ሰዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ቦታ እንዳላቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ የሚያከናውኑትን ሥራ እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል።

ፕሮግራሙ በሩሲያኛበእንግሊዝኛና በዩክሬንኛ በኢንተርኔት በቀጥታ ተላልፏል።

ሚያዝያ 9 | በኪየቭ የተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ

ፕሮፌሰር ፊሊፖቪች ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያዩ ሁኔታዎች ጋር ተስማምተው መኖር እንደሚችሉ አሳይተዋል። ከዚህም በላይ፣ የነበሩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለጥሩ ነገር በማዋል ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት ተጠቅመውበታል። . . . በሶቪየት አገዛዝ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያምኑበት ነገር በታማኝነት በመቆም በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችን አክብሮት አትርፈዋል።”

በዩክሬን ያለው የሃይማኖታዊ ሳይንስ ምርምር እና የዓለም አቀፍ መንፈሳዊ ግንኙነቶች ማዕከል ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ኢጎር ኮዝሎቭስኪ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “የአሁኑን ማንነታችንን ለመረዳት ያሳለፍነውን ታሪክ ማስታወስ አለብን። . . . የይሖዋ ምሥክሮች በግዞት የተወሰዱበትን ታሪክ አንዴ አስታውሰን ልንረሳው አይገባም። ይህ ታሪክ፣ በዩክሬን አጠቃላይ ታሪክ ውስጥ መካተት አለበት።” አክለውም “የሃይማኖት ምሁራን የይሖዋ ምሥክሮችንም ሆነ ሌሎች ሃይማኖቶችን በተመለከተ የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮችን እንዲሁም አሉባልታዎችን የማስወገድ ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል።

ይህ ፕሮግራም በእንግሊዝኛና በዩክሬንኛ በኢንተርኔት በቀጥታ ተላልፏል።