በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 30, 2019
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ኢዳይ የተባለው አውሎ ነፋስ ከደረሰ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ያከናወኑት መጠነ ሰፊ የእርዳታ ሥራ

ኢዳይ የተባለው አውሎ ነፋስ ከደረሰ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ያከናወኑት መጠነ ሰፊ የእርዳታ ሥራ

ኢዳይ የተባለው አውሎ ነፋስ መጋቢት 2019 የአፍሪካን ደቡብ ምሥራቃዊ ክፍል ከመታ በኋላ የማላዊ፣ የሞዛምቢክና የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ወንድሞች ለመርዳት ሲሉ 14 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን ወዲያውኑ አዋቀሩ። እስካሁን ድረስ ወንድሞቻችን በእነዚህ ሦስት አገሮች ውስጥ ጉዳት ከደረሰባቸው 1,434 የወንድሞቻችን ቤቶች መካከል 650 የሚሆኑትን በድጋሚ ገንብተዋል ወይም ጠግነዋል። ጉዳት ከደረሰባቸው 29 የስብሰባ አዳራሾች መካከል ስምንቱ በድጋሚ ተገንብተዋል፤ አሥሩ ደግሞ ጥገና ተደርጎላቸዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ3,500 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች በዚህ መጠነ ሰፊ የእርዳታ ሥራ ተካፍለዋል። ከእነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች መካከል አንዳንዶቹ በዚህ ሥራ ለመካፈል ሲሉ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። ከአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንዲሁም ከብራዚል፣ ከጣሊያን፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከፈረንሳይ የመጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች አሉ። ችሎታ ያላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ለአካባቢው ወንድሞች እንደ ግንበኝነትና አናጺነት ባሉት ሙያዎች ሥልጠና ሰጥተዋል።

የአንድ የግንባታ ቡድን አባላት በማላዊ ድጋሚ በመገንባት ላይ ባለ የጡብ ቤት ፊት ለፊት ሆነው

በሞዛምቢክ ኢዳይ የተባለው አውሎ ነፋስ የማንካን እና የሰፋላን ግዛቶች ሲመታ ወንድሞቻችን ከዘሩት ሰብል መካከል 70 በመቶው ወድሞ ነበር። በአካባቢው ያለው የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ በቅርንጫፍ ቢሮው አመራር ሥራ ሆኖ 430 ቶን ገደማ የሚሆን ምግብ አከፋፍሏል። ምግቡ የአካባቢውን ሰዎች አመጋገብ ግምት ውስጥ ያስገባ ሲሆን የበቆሎ ዱቄት፣ ባቄላ፣ ዘይት፣ ጨውና ስኳር ተከፋፍሏል። ከዚህም ሌላ አምስት ቶን የሚያህል የቲማቲም፣ የበቆሎ፣ የሩዝ እንዲሁም የሌሎች እህሎች ዘር ተከፋፍሏል።

የማላዊ ቅርንጫፍ ቢሮ የእርዳታ ሥራው የካቲት 2020 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚገመት የገለጸ ሲሆን በሞዛምቢክ የሚካሄደው የእርዳታ ሥራ ደግሞ ጥር 2020 እንደሚጠናቀቅ ተገምቷል፤ በዚምባብዌ የተካሄደው የእርዳታ ሥራ ግን መስከረም 2019 ተጠናቋል። ይህ መጠነ ሰፊ ሥራ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚፈጅ ይጠበቃል።

የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነውና በቅርንጫፍ ቢሮው የአደጋ ጊዜ እርዳታ ዴስክ የሚያገለግለው ወንድም ትሬንት ኤድሰን እንዲህ ብሏል፦ “ቤታቸው በድጋሚ የተገነባላቸው ወንድሞችና እህቶች በደስታ ፈንጥዘዋል። በቅርብም ይሁን በሩቅ የሚኖሩ ወንድሞች ያሳዩት ፍቅርና አሳቢነት ልብ የሚነካ ነበር። በርካታ ወንድሞች በሆነ መንገድ እርዳታ ማበርከት ፈልገው ነበር።”

በአውሎ ነፋሱ ከተጎዱት ከ10,000 የሚበልጡ የደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ ወንድሞችና እህቶች ጋር በመሆን ‘ለመከራ ጊዜ’ የሚሆኑ አፍቃሪ ወንድሞች ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—ምሳሌ 17:17

 

የእርዳታ ሠራተኞች በኮሎንጎንጆይ ጉባኤ ያሉትን የወንድም ዌሎስ ቤንዴራን እና የባለቤቱን የእህት ኤሲናራ ቤንዴራን ቤት በድጋሚ ገንብተውላቸዋል

በዚምባብዌ የሚኖሩት ወንድም ነኸሚያ ቲጌሬ እና ባለቤቱ እህት ፋቲማ ሴንጋሚ ቲጌሬ በድጋሚ በተገነባው ቤታቸው ፊት ለፊት ቆመው

በወረዳ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግሉት ወንድም ዊትነስ ጃቡ እና ወንድም ኦገስቲን ካማዚ ማላዊ ውስጥ በሚገኘው ንቻሎ መንደር ለሚኖሩ ቤታቸው የፈረሰባቸው ቤተሰቦች እረኝነት ሲያደርጉ

በዚምባብዌ ለሚኖሩ ወንድሞች የሚሰራጨው የበቆሎ ዘር በሺሞዮ የእርዳታ ማዕከል ከመኪና ሲወርድ

ወንድሞች ሞዛምቢክ ውስጥ በጠረፍ አካባቢ ለሚኖሩ ወንድሞች የእርዳታ ቁሳቁስ ለማድረስ ሺሬ ወንዝን በጀልባ ለመሻገር ተዘጋጅተው

ወንድሞችና እህቶች በማላዊ ከሚኖሩ ወንድሞች የተላኩ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል ወደሆነው በቴንጋኒ መንደር፣ ሞዛምቢክ ወደሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ ሲወስዱ

ወንድሞችና እህቶች በቴንጋኒ መንደር፣ ሞዛምቢክ ወደሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ መጥተው የእርዳታ ቁሳቁሶችን ሲወስዱ