በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዓለም አቀፋዊ ዜና

በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ክራይሚያ

በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ክራይሚያ

የሩሲያ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያደርሱት ከባድ ተቃውሞ ወደ ክራይሚያም ተዛምቷል። የሩሲያ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ ማኅበራት በማገድ ብቻ አልተወሰነም፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያከናውኑትን አምልኮ ለማደናቀፍ ቆርጦ እንደተነሳም በግልጽ አሳይቷል። ሚያዝያ 2017 ከተጣለው እገዳ አንስቶ የሩሲያ ባለሥልጣናት፣ በሩሲያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ በርካታ ድንገተኛ ብርበራዎች አድርገዋል፤ ይህን ተከትሎም ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በቁጥጥር ሥር ውለዋል እንዲሁም ታስረዋል። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተፋፋመው ይህ ዘመቻ በክራይሚያም ቀጥሏል።

ክራይሚያ ውስጥ የመጀመሪያው የብርበራ ዘመቻ የተካሄደው ኅዳር 15, 2018 በጃንኮይ ከተማ ነው፤ በወቅቱ ወደ 200 የሚጠጉ ፖሊሶችና ልዩ ኃይሎች በስምንት የይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያ ቤቶች ላይ ድንገተኛ ብርበራ አደረጉ፤ በወቅቱ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በትናንሽ ቡድኖች ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን እያነበቡና እየተወያዩ ነበር። ቢያንስ 35 የሚሆኑ መሣሪያ የታጠቁና ጭንብል ያጠለቁ ፖሊሶች የሰርጌ ፊላቶቭን ቤት ሰብረው ገቡ፤ ስድስት የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ ተሰብስበው ነበር። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በፖሊሶቹ የኃይል እርምጃ ተደናግጠው ነበር። ፖሊሶቹ አንድን የ78 ዓመት አረጋዊ ከግድግዳ ጋር ካጣበቁት በኋላ መሬት ላይ አስተኝተው በካቴና አሰሩት፤ በጣም ስለደበደቡት በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል መሄድ አስፈለገው። ሌሎች ሁለት በዕድሜ የገፉ ወንዶችም በሁኔታው በጣም ተደናግጠው ደማቸው ከፍ ስላለ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። የሚያሳዝነው፣ ቤቷ የተበረበረባት አንዲት ወጣት ፅንስ ተጨናግፎባታል።

ብርበራውን ተከትሎ ሰርጌ ፊላቶቭ የሩሲያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 282.2(1)ን መሠረት በማድረግ ‘የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴ አስተባብሯል’ የሚል ክስ ቀረበበት። መጋቢት 5, 2020 በክራይሚያ የሚገኘው የአውራጃ ፍርድ ቤት በሰርጌ ፊላቶቭ ላይ የስድስት ዓመት እስራት አስተላለፈ። ፍርዱ ከተላለፈ በኋላ ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት ተወሰደ።

በ2018 በጃንኮይ ከተካሄደው ብርበራ በኋላ ባሉት ዓመታት የልዩ ኃይል አባላት፣ በጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎች በመካፈል የተጠረጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ሰብረው መግባታቸውን ቀጠሉ። በቅርቡ ብርበራ የተካሄደው ግንቦት 22, 2023 ላይ ነው። ከንጋቱ 12:30 ከአሥር የሚበልጡ ፖሊሶች በፌኦዶሳ ወደሚገኝ ቤት ገቡ፤ አምስቱ ፖሊሶች መሣሪያ ታጥቀው ነበር። ፍተሻውን በሚያካሂዱበት ወቅት በቤቱ ውስጥ የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች ወለሉ ላይ እንዲተኙ አዘዟቸው። ፍተሻው ከሦስት ሰዓት በላይ የወሰደ ሲሆን ከወንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች አንዱን በቁጥጥር ሥር በማዋል ለምርመራ ወደ ሴቫስቶፖል ወሰዱት።

ከእነዚህ ፍተሻዎች በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የወንጀል ክሶች የተመሠረቱ ሲሆን ጥፋተኛ ናቸው ተብለው የተፈረደባቸውም አሉ፤ በአሁኑ ወቅት 9 የይሖዋ ምሥክር ወንዶች እስከ ስድስት ዓመት ተኩል የሚደርስ እስራት ተፈርዶባቸው ወህኒ ቤት ወርደዋል። ሁሉም የተከሰሱት የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴ አስተባብራችኋል በሚል ነው።

የጊዜ ሰሌዳ

  1. መስከረም 17, 2024

    በአሁኑ ወቅት ክራይሚያ ውስጥ 9 የይሖዋ ምሥክሮች ታስረዋል።

  2. ግንቦት 22, 2023

    ሕግ አስከባሪ አካላት በፌኦዶሳ የአንድን የይሖዋ ምሥክር ቤት ፈተሹ። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን የወረሱ ሲሆን አንድ የይሖዋ ምሥክር በቁጥጥር ሥር ዋለ።

  3. ነሐሴ 5, 2021

    ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ተፈተሹ። አሌክሳንደር ዱቦቬንኮ እና አሌክሳንደር ሊትቪንዩክ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

  4. ጥቅምት 1, 2020

    በሴቫስቶፖል ያሉ ዘጠኝ ቤቶች ተበረበሩ። ኢጎር ሽሚድት በቁጥጥር ሥር ውሎ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ።

  5. ሰኔ 4, 2019

    የልዩ ኃይል አባላት በሴቫስቶፖል የሚኖሩ አሥር የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። በኋላም፣ ቪክቶር ስታሺቭስኪ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎችን አደራጅቷል የሚል ክስ ተመሠረተበት።

  6. መጋቢት 20, 2019

    የልዩ ኃይል አባላት በአሉፕካ እና በያልታ የሚገኙ ስምንት ቤቶችን በረበሩ። አርተም ገራሲሞቭ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ ‘ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎችን አደራጅቷል’ በሚል ተከሰሰ።

  7. ኅዳር 15, 2018

    ከ200 የሚበልጡ ፖሊሶችና ልዩ ኃይሎች የሰርጌ ፊላቶቭን ጨምሮ በጃንኮይ የሚገኙ ስምንት ቤቶችን በረበሩ።