በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች የዛሬ 25 ዓመት watchtower.org የተባለውን ድረ ገጽ ለሕዝብ ክፍት አደረጉ። በ2012 JW.ORG አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ይህ ድረ ገጽ በዓለም ላይ በስፋት በመተርጎም ቀዳሚውን ቦታ ይዟል

ነሐሴ 17, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና

“ወንጌል በኢንተርኔት”

የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፉን የኢንተርኔት መረብ መጠቀም ከጀመሩ 25 ዓመታት ተቆጠሩ

“ወንጌል በኢንተርኔት”

የይሖዋ ምሥክሮች ኢንተርኔት ላይ ሕጋዊ ድረ ገጽ ካወጡ 25 ዓመታት ተቆጠሩ። የኅዳር 1997 የመንግሥት አገልግሎታችን “ወንጌል በኢንተርኔት” በሚል ርዕስ አማካኝነት watchtower.org የተባለ አዲስ ድረ ገጽ መውጣቱን አስተዋውቆ ነበር። ርዕሱ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “ማኅበሩ የይሖዋ ምሥክሮችን እምነትና እንቅስቃሴ የሚመለከቱ አንዳንድ ትክክለኛ መረጃዎችን ኢንተርኔት ውስጥ አስገብቷል። . . . የዌብ ሳይቱ ዓላማ አዲስ የሚወጡ ጽሑፎችን ማስተዋወቅ ሳይሆን ብዙ ሰዎች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝነት መረጃዎችን እንዲያገኙ መርዳት ነው።”

ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሰዎች አንዳንድ ትራክቶችን፣ ብሮሹሮችን እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት ላይ የወጡ ርዕሶችን ከ​watchtower.org ላይ ማውረድ ችለዋል። watchtower.org የተባለው ድረ ገጽ ለሕዝብ ክፍት የሆነው ጥር 15, 1997 ነው። ከዚያም በ1999 jw-media.org የተባለው ድረ ገጽ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። በዚህ ድረ ገጽ አማካኝነት ሕግ ነክ ጉዳዮችንና ሌሎች ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ክንውኖችን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃ መስጠት ተችሏል።

በ2005 jw.org አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በኋላም ከዚህ ድረ ገጽ ላይ የተወሰኑ ጽሑፎችንና የድምፅ ቅጂዎችን ማውረድ ተቻለ።

ነሐሴ 2012 ሦስቱም ድረ ገጾች በአዲስ መልክ በተዘጋጀው jw.org ውስጥ ተካተቱ። በአዲስ መልክ የተዘጋጀውን ድረ ገጽ አስመልክቶ የታኅሣሥ 2012 የመንግሥት አገልግሎታችን እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ከዓለም ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ኢንተርኔት ይጠቀማል። ኢንተርኔት ለብዙዎች በተለይም ለወጣቶች ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኗል። . . . የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት አጋጣሚው በጣም ጠባብ በሆነባቸው የምድር ክፍሎች ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹ እንዲደርሳቸው ያስችላል።”

JW.ORG ላይ የሚገኙት መረጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፤ አሁን ድረ ገጹ ላይ ጽሑፎችን፣ የድምፅ ቅጂዎችንና ቪዲዮዎችን ማግኘት ይቻላል። ቀደም ሲል ጽሑፎችን ማውረድ የሚቻለው በ411 ቋንቋዎች ብቻ ነበር። ድረ ገጹ በ2012 ተሻሽሎ ከወጣ ከሰባት ዓመት ገደማ በኋላ ግን ጽሑፎችን በ1,000 ቋንቋዎች ማውረድ ተችሏል፤ ከእነዚህ መካከል 100 የምልክት ቋንቋዎች ይገኙበታል። ይህ ድረ ገጽ በስፋት በመተርጎም ረገድ በዓለማችን የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል።

በተለይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ JW.ORG ይበልጥ ጠቃሚ መሣሪያ ሆኗል። በአካል የሚደረጉ ስብሰባዎች እንዲቆሙ በተደረገበት እንዲሁም ጽሑፎችን ማተምና ማሰራጨት ፈታኝ እየሆነ በሄደበት ወቅት ድረ ገጹን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ድረ ገጹን ከሚጎበኙ ሰዎች ጋር በተያያዘ ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በተከበረበት ዕለት ማለትም ሚያዝያ 7, 2020 ነበር፤ በዕለቱ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ድረ ገጹን ጎብኝተዋል። በ2020 ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች ድረ ገጹን የጎበኙ ሲሆን በ2019 ግን ድረ ገጹን የጎበኙት 800 ሚሊዮን ሰዎች ነበሩ። ከጥር 2022 ወዲህ በየቀኑ በአማካይ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ድረ ገጹን ይጎበኛሉ።

jw.org ላይ የሚወጣው ትክክለኛ መረጃ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ጭፍን ጥላቻ እንዲያስወግዱ በመርዳት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ለምሳሌ ቴኒሻ ጎርደን የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በቀላሉ መረጃ ማግኘት የሚቻል መሆኑ አስደስቶኛል፤ ማን እንደሆኑ፣ ምን ብለው እንደሚያምኑና እምነታቸው በምን ላይ የተመሠረተ እንደሆነ በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። ይህም ስለ እነሱ የነበረኝን የተሳሳተ አመለካከት ለማስወገድ ረድቶኛል።”

ቴኒሻ በ2017 ተጠመቀች። አሁን ጃማይካ ቤቴል ውስጥ በተመላላሽነት እያገለገለች ነው።

ቴኒሻ jw.org ላይ ትክክለኛ መረጃ ማግኘቷ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት አነሳስቷታል

ከድረ ገጹ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚከታተለው ዲፓርትመንት የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ክላይቭ ማርቲን እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ በሁሉም የዓለም ክፍሎች የሚኖሩና በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች እንዲሰሙ ለማድረግ jw.org​ን እንዴት እንደተጠቀመ ማየት በጣም የሚያስደስት ነው።”

ይህ ድረ ገጽ በስብከቱ ሥራ እገዛ ያደርግልናል፣ ከድርጅቱ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን ይሰጠናል እንዲሁም ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር አንድ በማድረግ ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል። ይህን ግሩም መሣሪያ ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—መዝሙር 145:1, 2