በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 30, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በዚህ ወረርሽኝ ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ የእምነት ባልንጀሮቻችንን እያጽናና ነው

ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በዚህ ወረርሽኝ ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ የእምነት ባልንጀሮቻችንን እያጽናና ነው

የይሖዋ ሕዝቦች ከዚህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ቢወስዱም አንዳንዶች በዚህ ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። (መክብብ 9:11) የሚያሳዝነው እስካሁን ድረስ 872 ወንድሞችና እህቶች በኮቪድ-19 ቫይረስ የተነሳ ሞተዋል። የእምነት ባልንጀሮቻችን ሐዘን የደረሰባቸውን ለማጽናናትና ለመደገፍ አፋጣኝ እርምጃ እየወሰዱ ነው። (1 ቆሮንቶስ 12:26) ከሁሉ በላይ ግን ወንድሞቻችን በፊልጵስዩስ 4:7 ላይ ‘የአምላክን ሰላም’ እንደሚሰጠን የገባውን ቃል እየፈጸመ ባለው በይሖዋ ይታመናሉ።

ወንድም ኡኑትዘርና ባለቤቱ

የይሖዋን ድርጅት ድጋፍ ያየችው አንዷ እህታችን በሰሜናዊ ጣሊያን በምትገኘው በቦልዛኖ ልዩ አቅኚ ሆና የምታገለግለው እህት ሃንቸን ኡኑትዘር ነች። የሚያሳዝነው፣ ባለቤቷ ወንድም ማንፍሬድ ኡኑትዘር መጋቢት 28, 2020 በኮሮና ቫይረስ የተነሳ ሕይወቱን አጣ። ወንድም ኡኑትዘር በልዩ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት 58 ዓመት ገደማ ያሳለፈ ሲሆን ባለቤቱም ለ54 ዓመት ያህል አብራው አገልግላለች። እነዚህ ባልና ሚስት ለ25 ዓመት ያህል በወረዳ ሥራ ተካፍለዋል። በተለያዩ አገሮች ውስጥ ያሉ ወደ 1,000 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ተከታትለዋል።

እህት ኡኑትዘር እንዲህ ብላለች፦ “ለወንድማማች ማኅበራችን ያለኝን አመስጋኝነት መግለጽ እፈልጋለሁ። ለአንድ ሰዓት እንኳ ብቻዬን አልተዉኝም። ፍቅራቸውን አትረፍርፈው ለግሰውኛል! የሚያስፈልገኝን ስሜታዊ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ እርዳታ ሰጥተውኛል። ወንድሞቼን በሙሉ በጣም እወዳቸዋለሁ።”

እህት ማሪያ ሆሴ ሞንካዳ እና ባለቤቷ ዳርዊንም በሐዘናቸው ወቅት የወንድሞችን ድጋፍ አይተዋል። እነዚህ ባልና ሚስት በኢኳዶር ተራሮች በኪችዋ ቋንቋ መስክ ያገለግላሉ። የሚያሳዝነው እህት ሞንካዳ በስድስት ቀን ልዩነት ውስጥ በኮቪድ-19 ምክንያት ሁለቱንም ወላጆቿን አጥታለች፤ እናቷ እህት ፋቢዮላ ሳንታና ጆርዳን 56 ዓመቷ ሲሆን በዘወትር አቅኚነት ታገለግል ነበር፤ አባቷ ወንድም ሪካርኮ ጆርዳን ደግሞ 60 ዓመቱ ሲሆን በጓያኪል በሚገኘው ፕራዴራስ ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ነበር። የእህት ሞንካዳ ሁለት ወንድሞችም በኮቪድ-19 ተይዘው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አገግመዋል።

ወንድም ሞንካዳና ባለቤቱ የጌታ ራት ሲያከብሩ

በሐዘን የተዋጠችው እህት ሞንካዳ ለአራት ሰዓት ተጉዛ ወደ ቤተሰቦቿ በመሄድ ልታጽናናቸውና የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በማደራጀት ልታግዛቸው ፈልጋ ነበር። ሆኖም እሷና ባለቤቷ ጉዳዩን በጸሎት ካሰቡበት በኋላ ወደ ጓያኪል መጓዛቸው ጥበብ እንዳልሆነ ወሰኑ። ከዚህ ይልቅ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ከዘመዶቿ ጋር ተገናኙ። እህት ሞንካዳ “ከዘመዶቻችን ጋር በአካል ብንገናኝ ኖሮ የእኛንም ሆነ የሌሎችን ጤንነት አደጋ ላይ እንጥል ነበር” ብላለች።

እርግጥ እህት ሞንካዳ ከፍተኛ “ሥቃይና ጭንቀት” እንደተሰማት ገልጻለች፤ ሆኖም እሷና ባለቤቷ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ማከናወናቸውን እንዲሁም ‘ይሖዋ አመራር እንዲሰጣቸው ሳያሰልሱ መጸለያቸውን’ ቀጠሉ። በተጨማሪም ለመታሰቢያው በዓል ዝግጅት አደረጉ፤ ይህን ያደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸውን በመጋበዝና ኢየሱስ ምድር ላይ ስላሳለፋቸው የመጨረሻ ቀናት የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በማንበብ ነው። ከዚህም ሌላ ደብዳቤ በመጻፍ በአገልግሎት መካፈላቸውን ቀጠሉ፤ እንዲሁም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የጉባኤ ስብሰባ ያደርጉ ነበር። ከእህት ሞንካዳ ዘመዶች መካከል ዘጠኙ ግብዣዋን ተቀብለው የመታሰቢያውን በዓል በስፓንኛ ተከታትለዋል።

እህት ሞንካዳ እንዲህ ብላለች፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ቀላል ባይሆንላቸውም የመታሰቢያውን በዓል ለመከታተል ዝግጅት ማድረጋቸው በጣም አበረታቶናል። በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ዘመዶቼ ስብሰባውን እንደተከታተሉ ማየቴም በጣም አስደስቶኛል።”

አክላም እህት ሞንካዳ እንዲህ ብላለች፦ “ያጋጠመን ነገር፣ ያለንበት ሁኔታ ምንም ያህል አስከፊ ቢሆን በይሖዋ አገልግሎት በቅንዓት መካፈላችን ሥቃዩን ለመቋቋም እንደሚረዳንና የይሖዋን በረከት እንደሚያስገኝልን አስገንዝቦናል።”

ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት የቤተሰባቸውን አባላት ካጡ ወንድሞቻችን ጋር አብሮ ያዝናል፤ እንዲሁም ይሖዋ ሐዘን ያጋጠማቸውን እንዲያጽናናቸው መጸለያችንን እንቀጥላለን። ይሖዋ ወረርሽኝን ጨምሮ ሥቃይ የሚያስከትሉብንን ነገሮች በሙሉ የሚያስወግድበትንና የሞቱ ታማኝ አገልጋዮቹን ሁሉ የሚያስነሳበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን።—1 ቆሮንቶስ 15:21, 22