በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በ1946 በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደውን “ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለ ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ የሚያሳይ ፎቶግራፍ

ነሐሴ 2, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የመጀመሪያው ትልቅ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ከተካሄደ ሰባ አምስት ዓመት ሞላው

“ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለው ታሪካዊ ስብሰባ ለቀጣዮቹ ስብሰባዎች ሞዴል ሆኗል

የመጀመሪያው ትልቅ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ከተካሄደ ሰባ አምስት ዓመት ሞላው

ነሐሴ 4, 2021 “ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ከተካሄደ 75 ዓመት ይሞላዋል፤ የይሖዋ ምሥክሮች ያካሄዱት የመጀመሪያው ትልቅ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ይሄ ነው። ይህ ስብሰባ የተካሄደው በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ ስታዲየምና በአቅራቢያው ባለ አዳራሽ ውስጥ ሲሆን የስብሰባው ቀን ደግሞ ከነሐሴ 4-11, 1946 ነበር።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ብዙም ሳይቆይ ወንድሞቻችን ይህን ስብሰባ አካሄዱ፤ ስብሰባው ዓለምን ካናወጠው ጦርነት ፍጹም ተቃራኒ ነበር። በስብሰባው ላይ ከዓለም ዙሪያ የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተሰብስበው ነበር። የዘር ክፍፍል በዩናይትድ ስቴትስ የተለመደ በነበረበት በዚያ ዘመን ከሁሉም ዘሮችና ባሕሎች የተውጣጡ ሰዎች በደስታ አንድ ላይ ተሰብስበዋል።

በአንድ ቦታ 80,000 የይሖዋ ምሥክሮች የተሰበሰቡበት የመጀመሪያው ስብሰባ “ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለው ስብሰባ ነበር። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጦርነቱ ወቅት ከሌሎች ተገልለው ከቆዩ በኋላ አንድ ላይ መሰብሰብ በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል። ከ32 አገሮች የመጡ 302 ልዑካን በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ማለትም እሁድ ላይ ወንድም ናታን ኖር “የሰላም መስፍን” የሚል ንግግር አቅርቦ ነበር።

“የሰላም መስፍን” የሚለውን የወንድም ኖርን የሕዝብ ንግግር የሚያስተዋውቅ ማስታወቂያ ከስታዲየሙ ውጭ ተሰቅሎ

ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ የተካሄደ ቢሆንም አንዳንድ እንቅፋቶች አጋጥመው ነበር። ስብሰባውን ያደራጁት ወንድሞች በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ላይ ከባድ ችግር አጋጥሟቸው ነበር። በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ የተሰበሰቡት ሰዎች ቁጥር ከአዳራሹ አቅም በእጅጉ በለጠ። ወንድሞች ለምሽቱ ፕሮግራም በቂ ቦታ ለማግኘት በአዳራሹ አቅራቢያ የሚገኘውን ስታዲየም መጠቀም ነበረባቸው። ፕሮግራሙ የሚጀምረው ከምሽቱ 1:45 ላይ ነበር፤ ሆኖም በዚያ ዕለት በስታዲየሙ ውስጥ ሁለት የቤዝቦል ጨዋታዎች እንዲካሄዱ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ጨዋታው የሚያበቃው ከምሽቱ 12:30 ላይ ነበር።

በሁለተኛው የቤዝቦል ጨዋታ ወቅት ነጎድጓዳማ ዝናብ ስለመጣ ጨዋታውን ሊታደም የተሰበሰበው ሕዝብ ጨዋታው ሳያበቃ በፊት ከስታዲየሙ ወጣ። በኋላ ግን የአየሩ ሁኔታ ተስተካከለ። በመሆኑም 50,000 የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ስታዲየሙ ገብተው በምሽቱ ፕሮግራም ላይ መካፈል ችለዋል።

ወንድም ኖር “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለው መጽሐፍ መውጣቱን ሲገልጽ

“ደስተኛ ሕዝቦች” በተባለው ስብሰባ ላይ ንቁ! የተባለ አዲስ መጽሔት እና “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለ የማስጠኛ መጽሐፍ መውጣቱ ተበሰረ። በተጨማሪም ወንድም ኖር በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን ማተሚያ ቤት እንዲሁም በሌሎች ስድስት አገሮች የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለማስፋፋት መታቀዱን ገለጸ።

ከስብሰባው ጉልህ ገጽታዎች አንዱ 2,602 ሰዎች ከአዳራሹ አቅራቢያ በሚገኘው በኢሪ ሐይቅ መጠመቃቸው ነው፤ በዚያ ዕለት 903 ወንድሞችና 1,699 እህቶች ተጠምቀዋል። በስብሰባው ላይ የመጠበቂያ ግንብ ጥናትና የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍሎች መቅረባቸው እንዲሁም 160 ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ሙዚቃ መቅረቡም የስብሰባው ጉልህ ገጽታዎች ነበሩ።

ከተጠማቂዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ለጥምቀት ተዘጋጅተው

ይህ ስብሰባ ለቀጣይ ስብሰባዎች ሞዴል ሆኗል። ለምሳሌ በዚህ ስብሰባ ላይ በርካታ የስብሰባ ዲፓርትመንቶች ተቋቁመዋል፤ ከእነዚህ መካከል አስተናጋጆች፣ የሊቀ መንበሩ ቢሮ፣ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ፣ የመስመር ዝርጋታ እና ጠፍተው የተገኙ ዕቃዎች የተባሉት ዲፓርትመንቶች ይገኙበታል።

አሁን በፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው በማኪስፖርት ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ሮን ሊትል ከአባቱና ከወንድሙ ጋር በዚያ ስብሰባ ላይ በተገኘበት ወቅት 11 ዓመቱ ነበር። ሦስቱም ስብሰባው በተካሄደባቸው ስምንት ቀናት በሙሉ የተኙት በአባትየው መኪና ውስጥ ነበር።

ወንድም ሊትል ንቁ! መጽሔት በወጣበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ በደንብ ያስታውሰዋል። እንዲህ ብሏል፦ “ንቁ! መጽሔት ሲወጣ ሁላችንም መጽሔቱን ይዘን እንሯሯጥ ነበር። መጽሔቱን ያልያዘ ሰው ካለ ደግሞ ሌሎቹ ይሰጡታል።”

ወንድም ሊትል አሁን 86 ዓመቱ ሲሆን በወቅቱ በጣም ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ተሰብስበው ማየቱ ምን ስሜት እንደፈጠረበት ያስታውሳል። እንዲህ ብሏል፦ “ስብሰባው ባያልቅ ብዬ ተመኝቼ ነበር። በጣም ደስ ይል ነበር!”

ይሖዋ ‘ቅዱስ ጉባኤዎቻችንን’ ስለሚባርክልን ከልብ አመስጋኞች ነን።—ዘሌዋውያን 23:2

 

ከነሐሴ 4 እስከ 11, 1946 በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደው “ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ፕሮግራም

የድምፅ ማጉያ የተሰቀለባቸውና “መጠበቂያ ግንብ እና መጽናኛ አንብቡ” የሚል ምልክት ያለባቸው ሁለት መኪናዎች። በበሩ ላይ የተለጠፈው ፖስተር “የሰላም መስፍን” የተባለውን የሕዝብ ንግግር የሚያስተዋውቅ ነው

ሁለት ሴት ልጆችና እናታቸው የድምፅ ማጉያ በተሰቀለበት መኪና ፊት ለፊት ቆመው። ልጆቹ በ1946 በተካሄደው “ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ላይ የወጣውን የንቁ! መጽሔት የመጀመሪያ እትም ይዘዋል። እናታቸው ደግሞ ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ የሚያሳትመውን ዘ ሜሴንጀር የተባለ ጋዜጣ ይዛለች

አንድ ወንድም ከሁለት ልጆቹ ጋር። በተሽከርካሪያቸው ላይ “የሰላም መስፍን” የሚለውን ንግግር የሚያስተዋውቁ ምልክቶች ተሰቅለዋል

በ1946 በተካሄደው “ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ላይ የተገኙ የስብሰባው ልዑካን “የሰላም መስፍን” የሚለውን የሕዝብ ንግግር የሚያስተዋውቁ በደረት ላይ የሚነገቡ ማስታወቂያዎችን ከመስክ አገልግሎት ክፍል ሲቀበሉ

በምግብ አገልግሎት ክፍል የሚያገለግሉ ወንድሞች

በ1946 በተካሄደው “ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ላይ የተገኙ ተሰብሳቢዎች በመመገቢያ አዳራሽ ውስጥ ሲመገቡ

በርካታ ተሰብሳቢዎች “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለውን አዲስ መጽሐፍ ይዘው

ወንድሞች ከስብሰባ አዳራሹ ውጭ ተሰብስበው፤ ብዙዎቹ በእምነታቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ ናቸው። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ (ከፊት በስተ ቀኝ) በመካከላቸው ይገኛል

የጥምቀት እጩዎች ከፊት ተቀምጠው

ጥምቀት የተካሄደበት ኢሪ ሐይቅ ከላይ ሲታይ