ታኅሣሥ 11, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ወደ ፓፒያሜንቶ ቋንቋ መተርጎም ከጀመረ 75 ዓመታት ተቆጠሩ
የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ፓፒያሜንቶ ቋንቋ መተርጎም ከጀመሩ ዘንድሮ 2023፣ 75ኛ ዓመታቸውን አስቆጥረዋል። ፓፒያሜንቶ በዋነኝነት በስፓንኛ፣ በደች እና በፖርቱጋልኛ ላይ የተመሠረተ ቋንቋ ነው። ኤቢሲ በመባል በሚታወቁት በአሩባ፣ በቦኔር እና በኩራሳው ደሴቶች የሚኖሩ ወደ 350,000 የሚጠጉ ሰዎች ፓፒያሜንቶ ቋንቋ ይናገራሉ።
በእነዚህ ደሴቶች የስብከቱ ሥራ የተጀመረው በ1920ዎቹ መገባደጃ ነበር። ከጊልያድ የተመረቁ ሚስዮናውያን በ1946 ወደ ኩራሳው በሄዱበት ወቅት በደሴቲቷ ላይ የተወሰኑ ጉባኤዎች ተቋቁመው ነበር። ሆኖም ወደ ፓፒያሜንቶ የተተረጎመ ምንም ጽሑፍ አልነበረም። የጉባኤ ስብሰባዎች በእንግሊዝኛና በፓፒያሜንቶ ቋንቋ ይካሄዱ የነበረ ሲሆን ወንድሞች የሚጠቀሙት በስፓንኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በደች የተዘጋጁ ጽሑፎችን ነበር። ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ፓፒያሜንቶ መተርጎም አስፈላጊ እንደሆነ ቢሰማቸውም በሥራው ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ የተለያዩ ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ በፓፒያሜንቶ የተዘጋጀ ምንም መዝገበ ቃላት ያልነበረ ከመሆኑም በላይ ቋንቋው የተወሰነ የሰዋስው ሕግም ሆነ የአጻጻፍ ሥርዓት አልነበረውም። ወደ ደሴቶቹ ከተመደቡት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን አንዱ የነበረው ወንድም ቢል የትስ በትርጉም ሥራው ድጋፍ አድርጓል። በ2002 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ እንደተገለጸው ወንድም ቢል እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “የመንግሥቱን መልእክት ስንተረጉም ከዚህ በፊት በፓፒያሜንቶ ተብለውም ሆነ ተጽፈው የማያውቁ ነገሮችን መግለጽ ወይም መጻፍ ነበረብን። ለትርጉሙ መሠረት የሚሆኑንን መሥፈርቶች ማውጣት ከባድ ነበር።” እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የነበሩ ቢሆንም ወንድሞች በትርጉም ሥራቸው ገፉበት።
ወደ ፓፒያሜንቶ የተተረጎመው የመጀመሪያው ጽሑፍ የሕዝቦች ሁሉ ደስታ የተባለው ቡክሌት ሲሆን የትርጉም ሥራው የተጠናቀቀው በ1948 ነበር። በኋላም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ጨምሮ ሌሎች ጽሑፎች ተተረጎሙ። በአሁኑ ጊዜ አዲስ ዓለም ትርጉም በፓፒያሜንቶ ደረጃ በደረጃ በመውጣት ላይ ይገኛል። መጀመሪያ የተተረጎመው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሩት መጽሐፍ ሲሆን ይህ መጽሐፍ የወጣው ጥቅምት 1, 2021 ነው።
በትርጉም ሥራ ረገድ የሚደረገው ትጋት የተሞላበት ጥረት በእነዚህ ደሴቶች በአስፋፊዎች ቁጥር ላይ ቀጣይ እድገት እንዲገኝ አስችሏል። በ1956 በፓፒያሜንቶ ቋንቋ የሚካሄደው የመጀመሪያው ጉባኤ ሲቋቋም በዚያ ጉባኤ ውስጥ 16 አስፋፊዎች ነበሩ። በዛሬው ጊዜ በፓፒያሜንቶ ቋንቋ በሚመሩ 25 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ1,600 የሚበልጡ አስፋፊዎች ይሖዋን በአንድነት እያመለኩ ነው። በ2023 ከ1,200 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል።
በፓፒያሜንቶ ቋንቋ መስክ የሚያገለግሉት በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብርሃናቸውን በማብራት ለይሖዋ ክብር ለማምጣት ጥረት እያደረጉ ነው፤ ይሖዋ ጥረታቸውን መባረኩን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—ማቴዎስ 5:16