በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሚዲያ ሥራዎች የሚከናወኑበት የራማፖ ሕንፃ ሲጠናቀቅ የሚኖረውን ገጽታ የሚያሳይ ምስል። ውስጠኛው ፎቶግራፍ፦ የራማፖ ከተማ የፕላን ቦርድ ሰኔ 28, 2023 ያደረገው ስብሰባ

ሐምሌ 3, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የዋናው መሥሪያ ቤት ፕሮጀክት በራማፖ

የራማፖ የግንባታ ፕሮጀክት ወሳኝ ፈቃድ አገኘ

የራማፖ የግንባታ ፕሮጀክት ወሳኝ ፈቃድ አገኘ

ሰኔ 28, 2023 በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የራማፖ የግንባታ ፕሮጀክት በጣም ወሳኝ ፈቃድ አገኘ። የራማፖ ከተማ የፕላን ቦርድ ለፕሮጀክቱ የተዘጋጀውን የግንባታ ንድፍ በአንድ ድምፅ አጸደቀ። ከዚህ በኋላ ብዙ መታለፍ ያለባቸው ሂደቶች ቢኖሩም አሁን የተገኘው ፈቃድ ፕሮጀክቱን ለመቀጠል የሚያስችል ነው።

የፕላን ቦርዱ ባደረገው ስብሰባ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆኑ ባለሥልጣናት ምንም ዓይነት ተቃውሞ አለማንሳታቸው የሚያስደስት ነው። በግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴ ውስጥ የሚሠራው ወንድም ኪት ካዲ እንዲህ ብሏል፦ “ለቦርዱ የምናቀርበውን የግንባታ ዕቅድ ለማዘጋጀትና የሚጠበቁብንን መሥፈርቶች ለማሟላት ለወራት ስንሠራ ቆይተናል። ግባችን ቦርዱ ላቀረብነው ማመልከቻ ፈቃድ መስጠት በተቻለ መጠን ቀላል እንዲሆንለት ማድረግ ነበር።” ቦርዱም ይህን ስላስተዋለ ለፕሮጀክቱ ያቀረብናቸውን ሐሳቦች በሙሉ በአንድ ድምፅ አጽድቋል። የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴው አባል የሆነ ዴቪድ ሶቶ የተባለ ሌላ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ጠቅላላ ስብሰባውም ሆነ ውሳኔ የመስጠቱ ሂደት ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቋል! የፕላን ቦርዱ አባላት በትጋት ላከናውኑት ሥራና ላሳዩን የትብብር መንፈስ ልናመሰግናቸው እንወዳለን። ከከተማው የፕላን ዲፓርትመንት ጋር ወደፊትም አብረን ለመሥራት እንጓጓለን።”

ይህ ፈቃድ በመገኘቱ በራማፖ ፕሮጀክት ላይ በርካታ ወሳኝ ሥራዎችን መጀመር ይቻላል። ወንድም ካዲ እንዲህ ብሏል፦ “የተቆረጡት ዛፎች ከአካባቢው ከተነሱ በኋላ የሕንፃ ሥራ ተቋራጮች የግንባታ ሥራቸውን መጀመር ይችላሉ። በቀጣዩ ዓመት መጨረሻ ላይ ደግሞ በግንባታ ፕሮጀክቱ ላይ መካፈል የሚፈልጉ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሥራ መጀመር ይችላሉ። ከቦርዱ ጋር ባደረግነው ስብሰባ ላይ ማመልከቻችን በሙሉ ድምፅ ፈቃድ እንዳገኘና በቅርቡ ሥራችንን መጀመር እንደምንችል ስንሰማ በጣም ነበር የተደሰትነው።”

በቅርቡ ላገኘው ለዚህ ወሳኝ ፈቃድ ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን ይሖዋን ያመሰግናል። በዚህ ፕሮጀክት ላይ በመካፈል ‘መልካሙን ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን እያበረቱ’ ያሉትን በሙሉ መባረኩን እንዲቀጥልም እንጸልያለን።—ነህምያ 2:18