በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቼልምስፎርድ፣ እንግሊዝ የሚገኙት የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች። ውስጠኛው ፎቶ፦ ወንድም ኬነዝ ኩክ የውሰናውን ንግግር ሲያቀርብ

ግንቦት 27, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ተወሰነ—በፕሮግራሙ ላይ ከ60 ከሚበልጡ አገራት የተውጣጡ ጎብኚዎች ተገኝተዋል

የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ተወሰነ—በፕሮግራሙ ላይ ከ60 ከሚበልጡ አገራት የተውጣጡ ጎብኚዎች ተገኝተዋል

ግንቦት 18, 2024 በቼልምስፎርድ፣ እንግሊዝ የሚገኙት የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች ተወስነዋል። የውሰና ንግግሩን ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ኬነዝ ኩክ ነው። የውሰና ፕሮግራሙን 1,518 ወንድሞችና እህቶች በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ በሚገኙ አራት የመሰብሰቢያ አዳራሾች ውስጥ ሆነው ተከታትለዋል። አንዳንድ የበላይ አካሉ አባላትና በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ረዳት ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል። በተጨማሪም ዝግጅቱ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በአየርላንድና በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ የትላልቅ መሰብሰቢያ አዳራሾችና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዕከላት የተላለፈ ሲሆን ይህም ሌሎች 10,085 ሰዎች ፕሮግራሙን እንዲከታተሉ አስችሏል። ቅርንጫፍ ቢሮው በተገነባበት ወቅት እገዛ ካበረከቱት 11,000 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች መካከል ከ3,000 በላይ የሚሆኑት በዚህ የውሰና ፕሮግራም ላይ ታድመዋል።

በሮዘርሃም፣ እንግሊዝ በሚገኘው ኢስት ፔኒን የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ የተገኙ ወንድሞችና እህቶች የውሰና ንግግሩን ሲከታተሉ

በቀጣዩ ቀን የተደረገው ልዩ መንፈሳዊ ፕሮግራም በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ ለሚገኙ 1,821 ጉባኤዎች በቪዲዮ ስርጭት የተላለፈ ሲሆን በድምሩ 172,834 ሰዎች ዝግጅቱን ተከታትለዋል።

የውሰናው ፕሮግራም ከመደረጉ በፊት በነበሩት የሳምንቱ ቀናት ውስጥ ግብዣ የተደረገላቸው እንግዶች የቅርንጫፍ ቢሮውን ሕንፃዎች ጎብኝተዋል። በቅርንጫፍ ቢሮው ክልልም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የስብከቱን ሥራ ለመደገፍና ጉባኤዎችን ለማጠናከር በቤቴል የሚከናወነውን ሥራ ለጎብኚዎች ለማሳየት አሳታፊ የሆኑ ኤግዚቢሽኖች ተካሂደው ነበር። ለምሳሌ የአካባቢ ቪዲዮ ቡድኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፊልም የሚዘጋጅበትን ሂደት ደረጃ በደረጃ ያሳየ ሲሆን ጎብኚዎች ቀረጻ እንዴት እንደሚካሄድ እንዲመለከቱ አድርጓል።

በስተ ግራ፦ አንዲት እህት መክሰስ እያቀራረበች። በስተ ቀኝ፦ የአካባቢ ቪዲዮ ቡድኑ ድርጅታችን የሚያዘጋጃቸው ቪዲዮዎች እንዴት እንደሚቀረጹ ሲያሳይ

ወንድሞችና እህቶች ለንደን፣ እንግሊዝ በሚገኘው ብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ የቂሮስ ሲሊንደርን ሲመለከቱ

ከእነዚህ ዝግጅቶች በተጨማሪ ወንድሞችና እህቶች ከቤቴል ውጪ ያሉ ሌሎች ቦታዎችን ጎብኝተዋል። ይህ ትምህርት ሰጪ ጉብኝት እንግሊዝ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳለፈውን ታሪክ ወደሚያሳዩ በለንደን ከተማ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችና ወደ ኬንት ወረዳ ጉዞ ማድረግን ያካትት ነበር።

የብሪታንያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሪቻርድ ኩክ ስላሳለፈው አስደሳች ሳምንት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከተለያየ የዓለም ክፍል የመጡ ወንድሞቻችን በዚህ ልዩ ዝግጅት ላይ ተገኝተው ማየት በጣም ያስደስት ነበር። ይሖዋ እንቅፋቶችን ሁሉ በአስደናቂ ሁኔታ በማስወገድ ለስሙ የሚመጥን የቅርንጫፍ ቢሮ ውሰና ፕሮግራም እንድናዘጋጅ ረድቶናል፤ ይህን ማየታችን እጅግ አስደንቆናል።”

እነዚህ ውብ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች ለአምላካችን ለይሖዋ በመወሰናቸው በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ ያሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ‘በጣም እንደተደሰቱ’ ሁሉ እኛም ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል።—ነህምያ 12:43