በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሰርቢያኛ እና በክሮሽያኛ መውጣቱን ሲያበስር

ሚያዝያ 29, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሰርቢያኛ እና በክሮሽያኛ ወጣ

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሰርቢያኛ እና በክሮሽያኛ ወጣ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሰርቢያኛ እና በክሮሽያኛ ቋንቋዎች መውጣቱን አስቀድሞ በተቀረጸ የቪዲዮ ንግግር አማካኝነት ሚያዝያ 25, 2020 አብስሯል። የሰርቢያኛው ትርጉም በሮማን እና በሲሪሊክ ፊደላት የተዘጋጀ ነው።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መንግሥታት ባወጡት ገደብ የተነሳ በሞንቴኔግሮ፣ በሰርቢያ፣ በቦስኒያ እና በሄርዘጎቪና እንዲሁም በክሮኤሺያ የሚገኙ ጉባኤዎች መጽሐፍ ቅዱሶቹ ሲወጡ አንድ ላይ መሰብሰብ አልቻሉም። ከዚህ ይልቅ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ልዩ የሆነ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በድምሩ 12,705 ሰዎች ስብሰባውን ተከታትለዋል።

በሰርቢያ እና በክሮኤሺያ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፕሮግራሙን ሲከታተሉ

ፕሮግራሙን ከተከታተሉት ወንድሞች አንዱ የተሻሻለውን መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ጌጥ” በማለት ጠርቶታል፤ “ይሖዋ በቀጥታ እያነጋገረኝ እንዳለ ተሰምቶኛል” ብሏል። የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል አንድ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “የተሻሻለውን መጽሐፍ ቅዱስ በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ሳነብ የይሖዋ ፍቅርና አሳቢነት ይበልጥ ግልጽ ሆነልኝ። ስለዚህ ወንድሞችንና እህቶችን ሳበረታታ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወዳቸውና እንደሚያስብላቸው ጥሩ አድርጌ ልገልጽላቸው እችላለሁ።”

የመጽሐፍ ቅዱሶቹ የትርጉም ሥራ የተጀመረው በ1996 ነበር። ከሦስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማለትም ሐምሌ 1999 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በሰርቢያኛ እና በክሮሽያኛ ወጣ። ከዚያም ከሰባት ዓመት በኋላ ማለትም በ2006 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሁለቱም ቋንቋዎች ወጣ።

ለመረዳት ቀላልና ትክክለኛ የሆነው የተሻሻለ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሰርቢያኛ እና በክሮሽያኛ መውጣቱ አንባቢዎች “የአምላክ ቃል ሕያው” መሆኑን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል ብለን እንተማመናለን።—ዕብራውያን 4:12