ሚያዝያ 28, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተካሄደ
በወረርሽኙ ምክንያት የ2021 የአገልግሎት ዓመት የአቅኚዎች ትምህርት ቤት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተካሂዷል፤ ትምህርት ቤቱ በዓለም ዙሪያ በዚህ መልኩ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው ነው። ተማሪዎቹ ለዚህ መንፈሳዊ ዝግጅት ካላቸው አድናቆት የተነሳ በትምህርት ቤቱ ለመካፈል የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ተሞክሮዎች፣ አንዳንድ አቅኚዎች በዚህ ረገድ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በይሖዋ እርዳታ እንዴት መወጣት እንደቻሉ ያሳያሉ።
በጃፓን የሚኖሩት እህት ሚዬኮ ዮሺናሪ ለ30 ዓመታት ያህል በዘወትር አቅኚነት አገልግለዋል። (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) እህት ሚዬኮ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን መጠቀም የሚከብዳቸው ከመሆኑም ሌላ አጥርተው ለማየት ይቸገራሉ፤ ያም ሆኖ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በሚደረገው የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ለመካፈል ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “በትምህርት ቤቱ ላይ ሐሳብ መስጠት እንድችል፣ ምርምር አድርጌ ያገኘኋቸውን ነጥቦች በትላልቅ ፊደላት ጽፌያቸው ነበር። ይሖዋ በዚህ ትምህርት ቤት አማካኝነት እንድታነጽና እንድበረታታ ረድቶኛል።”
በናይሮቢ፣ ኬንያ አቅራቢያ በምትገኝ ቲካ የተባለች መንደር የምትኖረው እህት አኒታ ካሪዩኪ ራሷን የምታስተዳድረው የግል ሥራ በመሥራት ነው። የውበት ባለሙያ የሆነችው ይህች አቅኚ እህት፣ በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ሥራዋን ለአንድ ሳምንት ያህል መዝጋት ነበረባት። መጀመሪያ ላይ ሁኔታው አሳስቧት የነበረ ቢሆንም ይሖዋ እንደሚረዳት ሙሉ በሙሉ ተማምና ነበር። “ይሖዋን ተማጽኜ ጉዳዩን ለእሱ ተውኩት፤ ከዚያም አገልግሎቴን ቀጠልኩ” ብላለች። አኒታ ትምህርት ቤቱ ከመጀመሩ በፊት ባሉት የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት አብዛኛውን ወጪዋን ለመሸፈን የሚያስችል ገንዘብ ማግኘት ቻለች። ሠላሳ የአሜሪካ ዶላር የሚያህል ገንዘብ ቢጎድላትም በትምህርት ቤቱ ተካፈለች። ረቡዕ ዕለት ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ አንዲት ደንበኛዋ ደወለችላት፤ ደንበኛዋ የደወለችው ዕዳዋን ለመክፈል ነበር። የሚገርመው ነገር፣ የከፈለችው ገንዘብ አኒታ ወጪዋን ለመሸፈን የሚያስፈልጋት ያህል ነበር!
በዮሮ፣ ሆንዱራስ የምትኖረው የእህት ሎሬን ማድሪጋሌስ መኖሪያ ቤት፣ ኤታ እና ሎታ በተባሉት ዝናብ የቀላቀሉ አውሎ ነፋሶች ምክንያት ተጥለቅልቆና አንድ ሜትር ገደማ ከፍታ ባለው ጭቃ ተሞልቶ ነበር። ሎሬን በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት እንድትካፈል በተጋበዘችበት ወቅት እሷና ቤተሰቧ ንብረታቸውን ሁሉ አጥተው እንዲሁም ለጊዜው ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ነበር። በመጋበዟ በጣም ብትደሰትም ትምህርት ቤቱ ከመጀመሩ በፊት ቤታቸውን አጽድተው መጨረስ የሚችሉ ስላልመሰላት ጉዳዩ አሳስቧት ነበር። ሎሬን እንዲህ ብላለች፦ “ማለዳ ጀምረን በጣም እስኪመሽ ድረስ እናጸዳ ነበር። ለቀናት ያህል በዚህ መልኩ ቀጠልን። በጣም ደክሞኝ ነበር። ለትምህርት ቤቱ መዘጋጀት የምችልበት አቅም እንደሌለኝ ስለተሰማኝ ግብዣውን መቀበል እንደማልችል ገለጽኩላቸው።” ሎሬን ጉዳዩ ምን ያህል እንዳሳዘናት ለይሖዋ በጸሎት ነገረችው። የሚገርመው ነገር፣ ትምህርት ቤቱ ከመጀመሩ ከጥቂት ቀናት በፊት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው አባላት ቤቷን ሊያጸዱላት መጡ። ይህም ዝግጅት የምታደርግበት ጊዜ እንድታገኝና ከቤቷ ሆና በትምህርት ቤቱ እንድትካፈል አስችሏታል።
በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ወንድም ስፔንሰር ስታሽ እና ባለቤቱ አሌግዛንድራ በአቅኚነት ያገለግላሉ። ብቻውን የሚኖረው የስፔንሰር አባት ሮበርት ትምህርት ቤቱ ከመጀመሩ በፊት ሆስፒታል ገባ። በዚህም የተነሳ ስፔንሰር እና ባለቤቱ በትምህርት ቤቱ መካፈል መቻላቸው አጠራጥሯቸው ነበር። ሮበርት ግን በትምህርት ቤቱ እንዲካፈሉ አበረታታቸው። የሚያሳዝነው፣ ትምህርት ቤቱ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊት ሮበርት በሞት አንቀላፋ። ስፔንሰር እና አሌግዛንድራ በጣም ቢያዝኑም ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ተካፈሉ። ወደ ይሖዋ አጥብቀው መጸለያቸው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥንካሬ ሰጥቷቸዋል። ስፔንሰር፣ አባቱ የፈለገውን ነገር ማድረጋቸው ውስጣዊ ሰላም እንደሰጣቸው ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ለአባቴ በትምህርት ቤቱ እንደተካፈልን ለመንገር እንዲሁም በዚያ ላይ ያገኘናቸውን አንዳንድ ነገሮች ለማካፈል እንጓጓለን። አብረውን የተማሩት ወንድሞችና እህቶች ብሎም አስተማሪዎቻችን የሚያስፈልገንን ድጋፍ አድርገውልናል።”
በደቡብ ኮሪያ የሚኖረው ወንድም ጆንግ ዴ ሺክ ላለፉት አሥር ዓመታት ያህል የኖረው በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ ነው። በጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ግማሽ አካሉ ሽባ ስለሆነ የሚንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር ነው። ወንድም ጆንግ ከዚህ በፊት በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ለመካፈል ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ባለበት የጤና ችግር ምክንያት ከአንድ ቀን በላይ መካፈል አልቻለም። በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በሚደረገው ትምህርት ቤት ላይ እንዲገኝ ሲጋበዝ በጣም ተደሰተ። እንዲህ ብሏል፦ “በተደረገው ዝግጅት በጣም ከመደሰቴ የተነሳ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። ይህ ዝግጅት ባይኖር ኖሮ በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈል የምችልበት ምንም መንገድ አልነበረም።” አክሎም “በዚህ ትምህርት ቤት መካፈል በመቻሌ ደስታዬ ወደር የለውም” በማለት ተናግሯል።
ወንድም ኤዲ ኤል ባዬህ እና ባለቤቱ ቼሪስ የሚኖሩት በኒው ሳውዝ ዌልስ፣ አውስትራሊያ ነው። ቼሪስ እንዲህ ብላለች፦ “አገልግሎቴን የማከናውነው በዘልማድ ነበር። ቅንዓቴን መጨመር የምችለው እንዴት እንደሆነ ግራ ገብቶኝ ነበር።” በአቅኚዎች ትምህርት ቤት መካፈሏ አመለካከቷን ለማስተካከል ረድቷታል። “ሁኔታዬ የተገደበ ቢሆንም እንኳ አገልግሎቴን ማስፋት የምችልባቸው የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ አስተዋልኩ” ብላለች።
ኤዲ ትምህርት ቤቱ እንዴት እንዳበረታታው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እቅፍ እንዳደረገኝ እንዲሁም ትከሻዬን መታ መታ እያደረገ ‘አይዞህ፣ በርታ! ከአንተ ጋር ነኝ፣ እወድሃለሁ ደግሞም አስብልሃለሁ!’ እንዳለኝ ተሰምቶኛል።”
በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የሚደረገው የአቅኚዎች ትምህርት ቤት በቀጣዮቹ ወራትም መካሄዱን ይቀጥላል። የትኛውም ፈታኝ ሁኔታ ይሖዋን ሕዝቡን ከማስተማር እንደማያግደው ማየት ምንኛ የሚያበረታታ ነው። ይህ ሁኔታ ኢዮብ “እነሆ፣ አምላክ በኃይሉ ከፍ ከፍ ብሏል፤ እንደ እሱ ያለ አስተማሪ ማን ነው?” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል።—ኢዮብ 36:22
ቀጥሎ ያሉት ፎቶግራፎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በተደረገው የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ የተሳተፉ በሌሎች አገሮች ያሉ አስተማሪዎችንና ተማሪዎችን ያሳያሉ።
አርጀንቲና፦ ተማሪዎች ቨርቹዋል ባክግራውንድ ተጠቅመው በሕዝብ መጓጓዣዎች ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ስለሚቻልበት መንገድ ሠርቶ ማሳያ ሲያቀርቡ
ካሜሩን፦ ለ12 ዓመታት ያህል በካሜሩን የአቅኚዎች ትምህርት ቤት አስተማሪና ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለው ወንድም ጋይ ሌተን፣ ከሙት ባሕር ጥቅልል ጋር ተመሳስሎ የተሠራን ጥቅልል ለተማሪዎች እያሳየ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሲያስተምር
ግሪክ፦ በማዕከላዊ ግሪክ ያሉ ጉባኤዎችን የሚጎበኘው ወንድም ታኪስ ፓዱላስ በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ሲያስተምር
ጣሊያን፦ በአገሪቱ በእንግሊዝኛ ከተካሄዱት አምስት የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤቶች አንዱ
ሜክሲኮ፦ በቅርቡ በጾጺል ቋንቋ (በዋነኝነት የሚነገረው በቺያፓስ ግዛት ነው) በወጣው የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት መማሪያ መጽሐፍ አማካኝነት ከተማሩት ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ። ሙሉው ፕሮግራም የአገሬው ቀደምት ተወላጆች በሚናገሩት በጾጺል ቋንቋ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው
ስሪ ላንካ፦ በልዩ አቅኚነት የሚያገለግሉት ወንድም ሲሻንታ ጉናቫርዳና እና ባለቤቱ ሺሮማላ በትምህርት ቤቱ ሲካፈሉ
ታንዛንያ፦ በዛንዚባር የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ዊልያም ቡንዳላ የዋይ-ፋይ አገልግሎቱ ይበልጥ ጠንካራ በሆነበት የግቢው ክፍል ተቀምጦ