ነሐሴ 9, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ለወንድም ሮስቶም አስላኒያን ፈረደ
በትራንስኒስትሪያ ለሃይማኖታዊ ነፃነት የተገኘ ድል
ሐምሌ 13, 2021 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሞልዶቫን እና ሩሲያን በሚመለከተው ጉዳይ ለወንድም ሮስቶም አስላኒያን ፈረደለት። ወንድም አስላኒያን በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ በትራንስኒስትሪያ (ፕሪድኔስትሮቭስካያ ሞልዳቭስካያ ሪፑብሊክ) የሚገኙ ባለሥልጣናት እስር ስለፈረዱበት አቤቱታውን ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቀረበ። ይህ ድል በትራንስኒስትሪያ ሃይማኖታዊ ነፃነት እንዲከበር መሠረት ይጥላል።
ትራንስኒስትሪያ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የሞልዶቫ ክፍል ሆና የምትቆጠር ቢሆንም በሁለቱ አገራት ስምምነት መሠረት ሩሲያም የአካባቢውን ደህንነት ትከታተላለች። ሁለቱም አገሮች የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን ስለሚቀበሉ የሕሊና ነፃነት የማክበር ግዴታ አለባቸው።
በ2010 ወንድም አስላኒያን ለውትድርና አገልግሎት የተመለመለ ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነቱ ምክንያት አማራጭ አገልግሎት ለማቅረብ ጥያቄ አቀረበ። መጋቢት 29, 2011 ጥያቄው ውድቅ የተደረገ ከመሆኑም ሌላ የአንድ ዓመት እስራት ተፈረደበት። ወንድም አስላኒያን የእስር ጊዜውን ያጠናቀቀ ቢሆንም ጉዳዩ ከጊዜ በኋላ ወደ አውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ተመራ።
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም የተላለፉ ውሳኔዎችን መሠረት በማድረግ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ፣ ወንድም አስላኒያን በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እሱን ለመቅጣት የሚያበቃ ምንም ሕጋዊ መሠረት እንደሌለ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ፣ ሩሲያ በትራንስኒስትሪያ ላይ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቁጥጥር ስለነበራት ለተፈጠረው ሁኔታ ኃላፊነት የምትወስደው ሞልዶቫ ሳትሆን ሩሲያ እንደሆነች ገልጿል። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ ባለሥልጣናቱ “ከምልመላ ለማምለጥ ሞክሯል” ብለው በወንድም አስላኒያን ላይ የአንድ ዓመት እስር መበየናቸው ሃይማኖታዊ ነፃነቱን እንደሚጋፋ ተናግሯል፤ በመሆኑም ለአንድ ዓመት በእስር በመቆየቱ የደረሰበትን ኪሳራ የሩሲያ መንግሥት ሙሉ በሙሉ እንዲከፍል ወስኗል።
በትራንስኒስትሪያ ለሚገኙ ወንድሞቻችን የሕግ ከለላ የሚሰጥ ውሳኔ በመደረጉ በጣም ተደስተናል። ይሖዋ በፈተና ውስጥ ላሉ ሕዝቦቹ ታማኝ ፍቅርና አሳቢነት እንደሚያሳይ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ አግኝተናል።—መዝሙር 18:25