በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስትራዝቡርግ፣ ፈረንሳይ የሚገኘው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት

መስከረም 29, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የአውሮፓ ፍርድ ቤት በሩሲያና በሊትዌኒያ ከአምልኮ ነፃነት ጋር በተያያዘ የመጨረሻውን ብይን አስተላለፈ

የአውሮፓ ፍርድ ቤት በሩሲያና በሊትዌኒያ ከአምልኮ ነፃነት ጋር በተያያዘ የመጨረሻውን ብይን አስተላለፈ

መስከረም 7, 2022 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተያያዘ በሁለት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻውን ብይን አስተላልፏል። ሰኔ 7, 2022 ፍርድ ቤቱ ሩሲያ በ2017 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የጣለችው እገዳ ሕገ ወጥ እንደሆነ ገልጾ ነበር። በዚያው ቀን ፍርድ ቤቱ፣ ሊትዌኒያ ከወንድም ስታኒስላቭ ቴሊያትኒኮቭ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን እንደጣሰች ገልጾ ነበር፤ ስታኒስላቭ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ የይሖዋ ምሥክር ነው።

ሩሲያም ሆነች ሊትዌኒያ ሰኔ 7 የተላለፈው ውሳኔ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻው ችሎት እንዲታይላቸው ይግባኝ አላሉም። በመሆኑም እነዚህ ሁለት አገራት ለተጎጂዎቹ አካላት ካሳ መክፈልን ጨምሮ የተጣለባቸውን ፍርድ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ታዘዋል።

ሰኔ 11, 2022 ሩሲያ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተፈጻሚ ላለማድረግ ስትል ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ራሷን አግልላለች። ያም ቢሆን ፍርድ ቤቱ፣ ሩሲያ ከመስከረም 16, 2022 በፊት ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ጋር በተያያዘ የፈጸመቻቸውን ጥሰቶች በተመለከተ የቀረቡ ክሶችን መመልከትና ብይን ማስተላለፍ ይችላል።

ሩሲያና ሊትዌኒያ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፋቸውን የመጨረሻ ብይኖች እንዲሁም የአምልኮ ነፃነት መብት እንዲያከብሩ መጸለያችንን እንቀጥላለን፤ ይህም ሰላም ወዳድ የሆኑ ክርስቲያኖች “ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በማደር . . . በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ” መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላል።—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2