በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ቪክቶር ስታሺቭስኪ

መጋቢት 30, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የክራይሚያ ፍርድ ቤት በወንድም ቪክቶር ስታሺቭስኪ ላይ የስድስት ዓመት ተኩል እስር ፈረደበት

የክራይሚያ ፍርድ ቤት በወንድም ቪክቶር ስታሺቭስኪ ላይ የስድስት ዓመት ተኩል እስር ፈረደበት

ወቅታዊ መረጃ፦ የሩሲያ ፍርድ ቤት የወንድም ቪክቶር ስታሺቭስኪን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

ነሐሴ 10, 2021 የሴቫስቶፖል ከተማ ፍርድ ቤት የቪክቶርን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። መጀመሪያ የተፈረደበት የስድስት ዓመት እስራት በዚያው ይጸናል። ጥፋተኛ ነው ተብሎ ከተፈረደበት ከመጋቢት 29, 2021 አንስቶ ከቆየበት ማረፊያ ቤት ወደ እስር ቤት በቅርቡ እንዲዛወር ይደረጋል።

በጋጋሪንስኪ አውራጃ የሚገኘው የሴቫስቶፖል ከተማ ፍርድ ቤት መጋቢት 29, 2021 ወንድም ቪክቶር ስታሺቭስኪ ጥፋተኛ ነው በማለት የስድስት ዓመት ተኩል እስር ፈርዶበታል። ቪክቶር ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት ተወስዷል። ቪክቶር ይግባኝ ይጠይቃል።

አጭር መግለጫ

ቪክቶር ስታሺቭስኪ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1966 (ካንስክ፣ ክራስናያርስክ ክልል፣ ሩሲያ)

  • ግለ ታሪክ፦ በ1983 ወደ ሴቫስቶፖል፣ ክራይሚያ ተዛወረ። በ1993 ከባሕር ኃይል ጡረታ ወጣ። በ2002 ከላሪሳ ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለት ሴቶች ልጆች አሏቸው። የጽንፈ ዓለም ውስብስብነትና የተደራጀ መሆኑ ሁልጊዜ ያስገርመው ነበር፤ በመሆኑም ፈጣሪን ለማወቅ ፍላጎት አደረበት። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ ሕይወቱ ትርጉም ያለው እንዲሆን ረድቶታል። በ2004 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

የክሱ ሂደት

ሰኔ 4, 2019 የፌደራል ደህንነት አባላት በሴቫስቶፖል የሚኖሩ አሥር የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። አንዳንዱ ፍተሻ እስከ አራት ሰዓት ድረስ የወሰደ ነበር። በፍተሻው ወቅት የፌደራል ደህንነት አባላቱ ለወንድሞችና ለቤተሰቦቻቸው ውኃ መጠጣትም ሆነ መጸዳጃ ቤት መጠቀም አልፈቀዱላቸውም። በተጨማሪም ባለሥልጣናቱ፣ ንብረታቸውን እንደሚያወድሙባቸው እንዲሁም ሕገወጥ የሆኑ ዕፆችን ቤታቸው በመደበቅ እንደሚያስይዟቸው በመዛት ወንድሞቻችንን ለማስፈራራት ሞክረዋል።

ከፍተሻው በኋላ ወንድም ቪክቶር ስታሺቭስኪ ተይዞ ሌሊቱን ማረፊያ ቤት እንዲያሳልፍ ተደረገ። “የጽንፈኛ ድርጅት መሪ” የሚል ክስ ተመሠረተበት። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ለፍርድ የቀረበው በሃይማኖታዊ እምነቱ የተነሳ ነው፤ ይህ ክስ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን በግልጽ የሚጥስ ነው።

ቪክቶር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብበትና የሚያሰላስልበት ቋሚ ፕሮግራም ያለው መሆኑ ደፋር እንዲሆንና በደስታ እንዲጸና እንደረዳው ገልጿል። በተለይ ደግሞ በመዝሙር 62:5-8 ላይ የሚገኘው ንጉሥ ዳዊት የተናገረው ሐሳብ ብርታት ሰጥቶታል። ቪክቶር ስለደረሰበት መከራ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ምንጊዜም ከጎኔ ስለሆነና ከማንም ይበልጥ ስለሚቀርበኝ ከእሱ ጋር ያለኝ ዝምድና ይበልጥ ተጠናክሯል። ይሖዋ የሚደርስብኝን መከራ እንዲሁም ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ለመሆን ያለኝን ፍላጎት እንደሚመለከት እርግጠኛ ነኝ፤ ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ለታላቅ ስሙ ሲል ከጠላቶቼ እንደሚያድነኝ እተማመናለሁ።”

ይሖዋ ቪክቶርን፣ ቤተሰቡንና ስደትን በጽናት እየተቋቋሙ ያሉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በሙሉ እንደሚደግፋቸው እርግጠኞች ነን። ይሖዋ ምንጊዜም መጠጊያና ምሽግ ይሆንላቸዋል።—መዝሙር 91:2