የካቲት 27, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የክራይሚያ ፍርድ ቤት በወንድም አርተም ገራሲሞቭ ጉዳይ ላይ ብይን ሊያስተላልፍ ነው
በክራይሚያ ሪፑብሊክ የምትገኘው የያልታ ከተማ ፍርድ ቤት የወንድም አርተም ገራሲሞቭን ጉዳይ ተመልክቶ መጋቢት 3, 2020 ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ፣ ወንድም አርተም ገራሲሞቭ በእምነቱ ምክንያት የስድስት ዓመት ተኩል እስራት እንዲበየንበት ጠይቋል።
ወንድም ገራሲሞቭ ተይዞ ምርመራ የተደረገበት መጋቢት 20, 2019 የፌዴራል ደህንነት አገልግሎት ፖሊሶች አሉፕካ እና ያልታ በተባሉት የክራይሚያ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ስምንት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ከፈተሹ በኋላ ነበር። ፖሊሶቹ ቤቶቹን በፈተሹበት ወቅት ኮምፒውተሮችን፣ ሌሎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሶችን ወስደዋል። መርማሪዎቹ ወንድም አርተም ገራሲሞቭ ከሌሎች ጋር ተሰብስቦ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመወያየቱ ምክንያት ብቻ ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎችን በማደራጀት ወንጀል ከስሰውታል።
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በእምነታቸው ምክንያት ብቻ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው “ደፋርና ብርቱ” ሆነው እንዲጸኑ ይሖዋ እንደሚረዳቸው ሙሉ እምነት አለን።—መዝሙር 138:3